ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ለኑሮ ተመራጭና እጅግ ሰላማዊ ነች በምትባለው ኒው ዚላንድ አንድ ፖሊስ መገደሉ መነጋሪያ ርዕስ ሆኗል።
ፖሊሱ መደበኛ አሰሳ እያደረገ አንድን ግለሰብ መኪናውን ሊያስቆም ሲሞክር ነበር ተተኩሶበት የሞተው፡፡ በተኩሱ የትራፊክ ፖሊስ የሆነ ሌላ ባልደረባውም ክፉኛ ቆስሏል።
በኒውዚላንድ የአንድ ፖሊስ መገደል አነጋጋሪ ዜና የሆነው እንዲህ አይነት ድርጊት ከጎርጎሳውያኑ 2009 ጀምሮ ተሰምቶም ተከስቶም ስለማያውቅ ነው ተብሏል።
የኒውዚላንድ ፖሊስ የተለየ ሁኔታ ከሌለ በስተቀር መሣሪያ አይዝም። ፖሊስ በሥራ ላይ ሳለ ተገደለ ሲባልም ከ11 ዓመታት በኋላ የትናንቱ የመጀመሪያ ሆኖ ተመዝግቧል።
ከ11 ዓመታት ወዲህ በግንቦት 2009 የተገደለው ሌላኛው የኒውዚላንድ ፖሊስም ቤት ለቤት መደበኛ አሰሳ ሲያደርግ ነበር፡፡
ሟቹን ባልደረባችንን በጸሎታችን እናስበዋለን፤ እጅግ አዝነናል ያሉት የፖሊስ አዛዡ አንድሩ ኮስተር፤ ሟቹ ፖሊስ በተሸከርካሪዎች ላይ አሰሳ በሚያደርግበት ወቅት ምንም ዓይነት መሣሪያ አልታጠቀም ነበር፡፡
በዚህ ዓመት በኒውዚላንድ ለ6 ወራት ብቻ ለልምምድ ያህል የታጠቁ ፖሊሶች ቡድን ተሰማርቶ እንደነበር ያስታወሱት ሓላፊው፤ የፖሊሶች አዛዥ አንድሩ ኮስተር ይህ ሥልጠና አሁን እንዳበቃና ኒውዚላንድ የፖሊስ ኃይሏ መሣሪያ አንጋች እንደማይሆን ማረጋገጫ ሰጥተዋል።