የአስከሬን ምርመራና የቀብር ክልከላን ጨምሮ በአስቸኳይ አዋጁ ላይ ማሻሻያ ተደረገ

የአስከሬን ምርመራና የቀብር ክልከላን ጨምሮ በአስቸኳይ አዋጁ ላይ ማሻሻያ ተደረገ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን  ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ባሉ አንዳንድ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ ተደረገ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በዛሬው እለት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መመሪያዎች ላይ ማሻሻያ መደረጉን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የሚዳረጉ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በማኅበረሰቡ የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም እንደሚቻልና ፤ ከዚህ ቀደም የአስክሬን የላብራቶሪ ውጤት ከመምጣቱ በፊት የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም አይቻልም የሚለውን መመሪያ እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።
ማሻሻያው ከላይ የተነሱትን ነጥቦች ለቀቅ ቢያደርግም፤ በቀብር ሥፍራ ላይ ከዚህ ቀደም የተቀመጠው 50 ሰዎች ብቻ ተገኝተው ሥርዓቱን ማከሄድ አለባቸው የሚለው መመሪያው አለመሻሻሉን ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።
የግሰለቦችን የአኗኗር ሁኔታ በተቀመጠው መመሪያ መሰረት አግባብ ከሆነ በቤታቸው እንዲቆዩ እንደሚደረጉም ያመላከቱት ዶክተር ሊያ፤
ከውጭ የሚገቡ ሰዎች ወደ አገር ከገቡ በኋላ ፣ ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ ከመጡበት አገር ተመርምረው ነፃ መሆናቸውን የሚያሳይ መረጃ ይዘው ከመጡ፤ ናሙና ተወስዶ በቤታቸው ለ14 ቀናት እንዲቆዩ እንደማደረግም ማሻሻያው ያሳያል።
በአንፃሩ ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋገጥ ሪፖርት ይዘው ለማይመጡ መንገደኞች ናሙናቸው ተወስዶ ለሰባት ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲቆዩ ይደረጋሉ ነው የተባለው። ይህም  ቀደም ሲል ለ14 ቀናት የነበረውን አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ወደ ለ7 ቀናት ብቻ እንዲሆን መወሰኑን ያመላክታል።

LEAVE A REPLY