የወላይታ ዞን ተወካዮች በደቡብ ክልል ም/ቤት ጉባዔ አለመገኘታቸው ታወቀ

የወላይታ ዞን ተወካዮች በደቡብ ክልል ም/ቤት ጉባዔ አለመገኘታቸው ታወቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና–  የሲዳማን የክልል አደረጃጀት ባፀደቀውና የትናንቱ የሀዋሳው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባዔ ላይ፤ የወላይታ ዞን ተወካዮች አልተሳተፉም ተባለ።

ተወካዮቹ ከስብሰባው ቀደም ብለው በልዩ ስብሰባ ላይ ላለመሳተፍ እንደወሰኑ የወላይታ ዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አበበች እራሾ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጻቸው አይዘነጋም።
በደቡብ ክልል ምክር ቤት ውስጥ ወላይታ ዞን 39 መቀመጫዎች  ያሉት ሲሆን፤ እነዚህ አባላት ትናንት በጉባኤው ላይ አልተገኙም።
የዞኑ ሕዝብ ለምክር ቤቱ ያቀረበው በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ተደማጭነት አላገኘም ፤ በሚል ምክንያት ነው የወላይታ ዞን ተወካዮች እየተካሄደ ባለው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ሳይሳተፉ የቀሩት።
የወላይታ ዞን ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በራሱ ክልል ሆኖ ለመደራጀት ጥያቄውን ቢያቀርብም ፤ ጥያቄው በተገቢው መንገድ ሳይታይ በመቅረቱ የተነሳ ለፌሬሽን ምክር ቤት ይግባኝ ማለታቸውን ተወካዮቹ ገልጸዋል።
 “የወላይታ ሕዝብ ጥያቄውን በተገቢው መልኩ ለክልሉ ምክር ቤትም ሆነ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን አስረድተው፤ ከአሁን በኋላ የወላይታ ብሔርን  የሚመለከቱ አጀንዳዎች ቢኖሩ በብሔሩ ምክር ቤት ካልሆነ፣ በፌደራል መስተናገድ አለባቸው እንጂ እኛ በሌለንበት በክልሉ ምክር ቤት መሆን የለበትም” ሲሉ አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ አበበች እራሾ የወላይታ ዞን ተወካዮች አቋም አሳይተዋል።
የወላይታ ብሔርን በክልል የመደራጀት ጥያቄ በተመለከተ ከአንድ ዓመት በፊት ነው ለደቡብ ክልል ምክር ቤት ያቀረብነው ያሉት አፈ ጉባዔዋ ፤ ያንን ጥያቄ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መመለስ እንደነበረበትና ሥልጣኑም እስከዚያ ድረስ ከመሆኑ ባሻገር ሪፍረንደም ማደራጀት ቢሆንም ይህንን ሊያደርግ አልቻለም ሲሉ ገልፀዋል።
በእንዲህ ዓይነት ምክንያቶች በዞኑ ውጥረት እንደነበር ያስታወሱት የሲዳማ ዞን ተወካዮች፤ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች በሕጋዊ መንገድ ይመለሳሉ በሚል ተስፋ፣ እስከ ታህሳስ 10/2012 ድረስና ጉዳዮ አንድ ዓመት እስኪሆነው ብንጠብቅም ምንም ምላሽ አልተገኘም ይላሉ።
 ” የእኛ ዞን (የብሔሩ ተወካዮች ) በክልሉ ምክር ቤት ወደ 39 መቀመጫ ነው ያለው። በተለያዩ ጊዜያት በተገኙ አጋጣሚዎች፣ በተደረጉ መደበኛ ያልሆኑ ጉባዔዎች ጭምሮ  አጀንዳው እንዲቀርብ በጽሑፍ የአሠራር ደንቡ በሚፈቅደው መሰረት ጠይቀናል።  ግን የሕዝባችንን ድምጽ ለመስማት ፍላጎት የለም” ያሉት ተወካዮቹ ከዚህ የተነሳ  በክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ላለመሳተፍ እንደወሰኑ ገልፀዋል።

LEAVE A REPLY