ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ግብፅ በአባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ያላት ምርጫ ከኢትዮጵያ ጋር መተባበር ብቻ እንደሆነ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ገለፁ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህር፣ የአባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪና ተደራዳሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ፤ ” ለግብፅ ሌላ አማራጭ ማማተር ከንቱ ነው፡፡ ግብፅ፣ ሱዳን ወይም የትኛውም ሌላ ወገን ማወቅ ያለበት እ.ኤ.አ ከ2015 የመርህ መግለጫ ሰነድ በስተቀር ኢትዮጵያ ከግብፅም ሆነ ከሱዳን ጋር አስገዳጅ ውለታ እንደሌላት ነው፡፡ በአባይ ውሃ የኢትዮጵያ መብት፣ ከግብፅ የተረፈ መሆን የለበትም” ሲሉ ሁለቱ ሀገራት በህዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ የገቡትን ውዝግብ አስመልክቶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ሐሳባቸውን በግልፅ አስቀምጠዋል።
ከዚህ ውጭ የሆነ አካሄድ ኢትዮጵያ የውኃ መብት ሉዓላዊ ባለቤትነት እንዳይኖራት ያደርጋል ያሉት ባለሙያው፤ እስከ ዛሬም ድረስ ግብፅ የምትሄድበት መንገድ የማይገባት አካሄድ መሆኑ መታወቅ እንዳለበትም ገልጸዋል።
“የአባይ ውሃ ከኢትዮጵያ ይነሳል ፤ ለወደፊቱም እንዲሁ ይቀጥላል። ድንበር ተሻጋሪ ሀብት ስለሆነ በመተሳሰብና በመተባበር በውሃ ሀብቱ ሁሉም መጠቀም ይችላል” የሚሉት ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ፤ “በመሆኑም የግብፅ ፍላጎት የሌሎች ውሃ ተጋሪዎች ጥቅም፣ መብትና የልማት ፍላጎት ሊረመርም አይገባም፤ አይችልምም። ምንጊዜም ቢሆን የግብፅ ፍላጎት በጉልበት ሌሎች ላይ ሊጫን አይችልም። በጦርነትም አይሆንም ” ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ለግብፅ የተሳሳተ ፍላጎት ሲባል ጥቅማቸውን ዘንግተው፣ እጃቸውን አጣጥፈው፣ መብታቸውን ጥለው ይቀመጣሉ ተብለው እንደማይቀመጥም የገለጹት ፕሮፌሰሩ፤ ግብፅ በጦርነት ፍላጎቷን ለመጫን ስንት ጦርነት ትዋጋለች? ስንት ጊዜስ ትዘምታለች? የግብፅን ጦርነት በትህትና የሚያስተናግድስ ማንን ታገኛለች? ሲሉም ጠይቀዋል።