ላሊበላ፣ ኮረም ፣ አላማጣ፣ ቡሬ፣ አገው፣ ጋይንት፣ ቤጊና እንጅባራ ከተሞች ቀለበታማው ግርዶሽ...

ላሊበላ፣ ኮረም ፣ አላማጣ፣ ቡሬ፣ አገው፣ ጋይንት፣ ቤጊና እንጅባራ ከተሞች ቀለበታማው ግርዶሽ ታየ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ዛሬ ሰኔ 14/ 2012 ዓ.ም ጠዋት ታይቷል።

በከፍተኛ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው  ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ እንደሚታይ ነው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዛሬ በላልይበላ አካባቢዎች ጨለምለም ብሎ የነበረ ሲሆን፣ ቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሹም መታየቱ ተሰምቷል። በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ፀሐይ ከ80 በመቶ ተሸፍና በከፊል ግርዶሽነት የታየች ሲሆን ፤ በተወሰነው የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል ደግሞ ፀሐይ ከ60- 80 በመቶ ተሸፍና ግርዶሹ ታይቷል።
ዋናው ግርዶሽ  ከምዕራብ ኢትዮጵያ አንስቶ እስከ ሰሜን ምስራቅ ድረስ የሚዘልቀው መሆኑን የጠቆመው የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ ክስተቱም ወለጋ ጀምሮ፣ በከፊል ጎጃምንና ጎንደርን አቆራርጦ ፤ ወደ ወሎ በመሻገር ላሊበላንም ያዳረሰ እንደሆነም አስታውቋል።
በተጠቀሱት ሥፍራዎች ፀሐይ እስከ 98 በመቶ ተሸፍና ቀለበታዊውን ግርዶሽ ማየት ተችሏል።  ላሊበላን ጨምሮ ቆቦ፣ ኮረም፣ አላማጣ፣ ቤጊ፣ ሜቲ፣ እንጅባራ፣ ቡሬ፣ አገው ግምጃ ቤት፣ጋይንት፣ ንፋስ መውጫ፣ ግሽ አባይ ከተሞች ቀለበታዊውን ግርዶሽ ካዮት መካከል ይጠቀሳሉ።
ግርዶሹ ከጥዋቱ 12፡45 ጀምሮ እስከ ስድስት ሰዓት ተኩል የቆየ እንደነበርም ተነግሯል። ቀለበታዊ ግርዶሽ የሚከሰተው ጨረቃ በፀሐይና በምድር መካከል ስትሆን፣ እንዲሁም ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ተጋርዳ ብርሃን መስጠት ሳትችል መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።
ጨረቃ በፀሐይና መሬት መካከል ስትሆን የሚፈጠረውንም ክስተት ለማየት በርካቶች ወደ ላልይበላ ተጉዘዋል።
ይህን መሰል ታሪካዊ ክስተት በድጋሚ የሚያጋጥመው ከ18 ዓመታት በኋላ ሲሆን፤ ሙሉ የፀሐይ ግርዶሽ የሚኖረው ከ146 ዓመታት በኋላ እንደሆነ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መግለጹ አይዘነጋም።
ዛሬ በተወሰኑ የኢትዮጵያ ከተሞች የታየውጰቀለበታዊ የፀሐይ ግርዶሽ ከኮንጎ ተነስቶ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያንና ኤርትራን አዳርሶ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የሚሻገር መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

LEAVE A REPLY