በሺኅዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ አህዮች ለእርድ ወደ ኬንያ እየተጓዙ ነው ተባለ

በሺኅዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ አህዮች ለእርድ ወደ ኬንያ እየተጓዙ ነው ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በርካታ የኢትዮጵያ አህዮች  በሕገ ወጥ መንገድ ለእርድ ወደ ኬንያ እየተጓጓዙ ናቸው ተባለ።

እነዚህ በሺኅዎች የሚቆጠሩ አህዮች በቆዳቸው ምክንያት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ  መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
 ጎረቤት ሀገር በሆነችው ኬንያ የአህያ እርድ ዳግም መፈቀዱን ተከትሎ ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አህዮች በየቀኑ በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ እየተወሰዱ መሆኑ ተሰምቷል።
የአህያ ቆዳን በመቀቀል ” ኤህጌዮ “ተብሎ የሚጠራ የሚሠራ መሆኑና፤ ይህ ጄል ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያወጣም እየተነገረ ነው።
“በብዙ ዶላር ነው የሚሸጠው፤ በርካታ ሰዎች ስለሚፈልጉት ዋጋው በጣም ጨምሯል። የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል በርካታ አህዮች እየታረዱ ነው” ነው ሲሉ በኢትዮጵያ “ዘ ዶንኪ ሳንክቱአሪ” ሓላፊ ዶ/ር ቦጂዓ ኢንዳቡ ክስተቱን ለማስረዳት ሞክረዋል።
ኤህጌዮ ጄል፤ በሞቀ ውኃ ወይም በአልኮል ሊበጠበጥ እንደሚችል፣ በተጨማሪም የምግብ እና መጠጥ ግብዓት ከመሆኑ ሌላ፣ የፊት ክሬም ያሉ የመዋቢያ ምርቶች ለማዘጋጀትም እጅግ ተፈላጊ ግብዓት መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
 አህዮች ከኢትዮጵያ በሕገ ወጥ ምክንያት መውጣት ከጀመሩ ቆይቷል የሚሉት ዶ/ር ቦጂዓ ፤ ይህ ድርጊት በአገሪቱ በሚገኙ የአህያዎች ቁጥር ላይ ከሚያሳድረው አሉታዊ ጫና በተጨማሪ፣ የአህዮች ቁጥር መመናመን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶችን  ያስከትላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ 9 ሚሊዮን አህዮችን በመያዝ በዓለማችን ቁጥር አንድ በርካታ አህዮች የሚገኙባት አገር እንደሆነች “ዘ ብሮክ” የተሰኘው የአህዮች ተንከባካቢ ድርጅት ሓላፊ አቶ ደስታ አረጋ ገልጸዋል።
 “ኤህጌዮ” የተሰኘው መድኃኒት ያለውን ፍላጎት ለማሟላት 5.6 ሜትሪክ ቶን የአህያ ቆዳ ያስፈልጋል። በዚህም የበርካታ አህዮች መገኛ የሆነችውን ኢትዮጵያ ዒላማ ውስጥ እንድትገባ ያደረጋት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
 ቀደም ሲል በቢሾፍቱ እና አሰላ ከተሞች ተከፍተው የነበሩት የአህያ እርድ ማከናወኛ ማዕከላት በአካባቢው ነዋሪዎች ቁጣ መዘጋታቸው አይዘነጋም። በኬንያም እንዲህ ዓይነት ክልከላ የነበረ ቢሆንም ፣ የአህያ እርድ በቅርቡ ሕጋዊ ፍቃድ አግኝቶ ሥራው በተግባር ላይ ውሏል።
በኬንያ ባሉ አራት የአህያ እርድ ማከናወኛ ቄራዎች ውስጥ በየቀኑ 1ሺኅ 200 የሚሆኑ አህዮች የሚታረዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት ከኢትዮጵያ የሚሄዱ መሆናቸው ታውቋል።

LEAVE A REPLY