ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በግብፅ የሚገኙ የመረጃ መረብ ሰርሳሪዎች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ተቋማት የመረጃ መረብ መዋቅር ላይ ጥቃት ለማድረግ እንደሞከሩ የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ገለፀ።
በሦስት የተለያዩ ቡድኖች አማካይነት የተሞከረው የመረጃ መረብ ጥቃት በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናን ለመፍጠር ያለሙ መሆናቸውን ኤጀንሲው አስታውቋል።
የጥቃት ሙከራ ባደረጉት ቡድኖች ላይ ክትትል ሲያደርግ እንደቆየ ያስታወሰው ኤጀንሲው በተለይ ባለፈው አርብና ቅዳሜ ከፍተኛ የመረጃ መረብ የጥቃት ሙከራዎች ማድረጋቸውንና በኤጀንሲው አማካይነት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አረጋግጧል።
በዚህም የጥቃት ሙከራ 13 የመንግሥት፣ 4 መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን የድረ-ገጾች ዒላማ በማድረግ ለማስተጓጎል ሙከራ መደረጉን የጠቆመው መግለጫ ተቋማቱ እነማን እንደሆኑ ከመግለጽ ግን ተቆጥቧል።
ይህ የመረጃ መረብ ጥቃት ሙከራው የተደረገው ‘ሳይበር ሆሩስ ግሩፕ’፣ ‘አኑቢስ ዶት ሃከር’ እና ‘ሴኪዩሪቲ ባይ ፓስ’ በተባሉ መረጃ መረብ ሰርሳሪ ቡድኖች ናቸው።
በአገሪቱ ባሉ ተቋማት የመረጃ መረብ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሞክረዋል ያላቸው ቡድኖች ላደረጉት ሙከራ ሓላፊነቱን መውሰዳቸውንና ዓላማቸውም ኢትዮጵያ እየገነባቸው ካለው ከህዳሴው ግድብ ጋር የተያያዘ መሆኑን መግለጻቸውን ተቋሙ በማያያዝ ይፋ አድርጓል።