ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በቄለም ወላጋ ዞን አምፊሎ ወረዳ ሸበል ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ሰዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት መፈናቀላቸውን ተከትሎ በጋምቤላ ለመጠለል መገደዳቸውን ገለጹ።
ከአንድ ሳምንት በፊት በቀበሌያቸው ሸበል፣ በተከሰተው ግጭት የተነሳ የአምስት ሰዎች ሕይወት ካለፈ በኋላ ወደ ጋምቤላ ክልል እንደሸሹ ለቢቢሲ የተናገሩትና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ነዋሪ፤ “አሁን ደግሞ የመንግሥት ሓላፊዎች በጉልበት ወደ መኖሪያ ቀያችን መልሰውናል” ሲሉ አማርረዋል።
የሁለት ልጆች አባት የሆነውና ሸራ ወጥሮ በጋምቤላ 03 እንዳለ የሚናገረው ሌላኛው ተፈናቃይ በበኩሉ፤ አሁንም ቢሆን በፍርኃት እንደሚኖር ጠቁሞ ወደ መኖሪያ አካባቢው የተመለሰው ያለው ሁኔታ ስለሚያሰጋው መሆኑን አስታውቋል።
“ቅዳሜ ጠዋት ሸበል ውስጥ ከፍተኛ ተኩስ ሰሲማ ደንግጠን ተበታተንን” ያሉ ወደ ቀያቸው ከተመለሱት መካከል አንዱ ግለሰብ ስለሁኔታው ሲያስረዱ፤ “የመንግሥት ወታደሮች የሚሉት ተኩሱ የተከፈተው የሸኔ ታጣቂዎች ላይ ነው። እኛ ወደ ጫካ የሸሸነው ተኩሱን ሰምተን ነው። የቡና ጫካችን ውስጥ ሆነን ስንሰማ በዚህ ተኩስ የተነሳ አምስት ሰዎች መሞታቸውን ተረድተናል” ብለዋል።
ይህንን ፈርተን በእግራችን ወደ ጋምቤላ ለመጓዝ ተገደናል ሲሉ የገለጹት የምዕራብ ወለጋ ነዋሪ፤ ችግሩ በተከሰተበት ዕለት ሁሉም ነዋሪዎች ደንግጠው መሸሻቸውን ጠቁመው፤
“ተኩስ ሲከፈት እየሞተ ያለው ሰላማዊ ሰው ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
በእግራችን ሰባት ሰዐት ተጉዘን ነው ጋምቤላ የገባነው የሚሉት እነኚህ ተፈናቃዮች ለሊቱን ተጉዞ በነጋታው ጋምቤላ 03 የሚባለው አካባቢ ደርሰው በሥፍራው ላስቲክ ወጥረው እንደሰፈሩ፣ የክልሉ መንግሥትና ሕዝብም በፀጋ ተቀብሎ የምግብ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ጠቁመው፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ግን አሁን ላይ አብዛኛውን ተፈናቃይ በግድ ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እያደረጉ መሆኑን ይናገራሉ።
ወደ ትውልድ ቀዬው መመለስ የማይሻ ማንም ሰው የለም የሚሉት የወለጋ ተፈናቃዮች አሁን ያለው የሥፍራው ሰላም አስተማማኝ ባልሆነበት ሁኔታ ለፖለቲካ ትርፍ ብቻ የሚደረግ ማስመለስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።