ጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ሦስቱ ሀገራት በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም  ግልፅ የሆነ ድርድር...

ጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ሦስቱ ሀገራት በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም  ግልፅ የሆነ ድርድር እንዲያደርጉ አሳሰቡ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ስምምነት ላይ ያልደረሰቡትን የዓባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም  አስመልክቶ መግለጫ አወጡ።

“ሲቢኤስ” የሚል ቅፅል መጠሪያ ያለው የጥቁር አሜሪካውያን የኮንግረስ አባላት ኮውከስ፤ ሦስቱ ሀገራት በመሀላቸው ያለውን ጡዘት እንዲያረግቡት ጥያቄ አቅርቦ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ትብብራቸውን እንዲቀጥሉበትና ችግራቸውን በድርድር እንዲፈቱ አስጠንቅቋል።
ሀገራቱ በጋራ ተጠቃሚነት ተማምነው በዓለም ዐቀፍ ሕጎች መሠረት በመጓዝ ከመፍትኄ እንዲደርሱና ሁሉንም ነገር በሠለጠነ መንገድ እንዲፈቱም ኮንግረሱ መልዕክት አስተላልፏል።
የጥቁር አሜሪካውያን ኮንግረስ አባላት ኮውከስ ዩናይትድ ስቴትስና ሌሎች ዓለም ዐቀፍ አካላት በ2015 ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የገቡትን የስምምነት ሰነድ እንዲያከብሩ ጠይቆ፤ እነኚህ አካላት ጉዳዩን ከአፍሪካ ህብረትና በቀጠናው ከሚገኙ ዲፕሎማቶች ጋር በመተባበር ለመፍታት ጥረት ሊያደርጉም ይገባል ተብሏል።
ከምንም በላይ የአፍሪካ ህብረት በሦስቱ ሀገራት መካከል የሚደረገው ሰላማዊ ስምምነት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ አንድ ወገንን ብቻ የሚጠቅም አለመሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባው መግለጫው ጠቁሟል።
“የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት የዓባይ ወንዝ ፍሰት፣ የኃይል አቅርቦት እንዲሁም በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የምግብ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ አለው። የግብፅ ሕዝብ ቁጥር 100 ሚሊየን እየተጠጋ በመሆኑ የሕዳሴው ግድብ በናይል ወንዝ ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ ለግብፅ ሕዝብ የተሻለ የውኃ አቅርቦት ሊያመጣ ይችላል። ኢትዮጵያ ደግሞ 20 በመቶ ሕዝቧን ሊጎዳ ይችላል ተብሎ የተገመተ የድርቅ አደጋ ተደግኖባታል።
 አልፎም በቅርቡ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከ32 ሺኅ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሰፈረ ሰብል ጎድቷል። በሌላ በኩል ሱዳን ከሕዳሴው ግድብ ልትጠቀም ትችላለች። ግድቡ የውሃ ፍሰትን ይመጥናል፣ ደለል ያስቀራል፣ የግብርና ፕሮጀክቶቹን ያስፋፋል፣ እንዲሁም ከውሃ የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ይሰጣታል።” ሲል የጥቁር አሜሪካውያን የኮንግረስ አባላቱ መግለጫ የህዳሴው ግድብ ጥቅምን በመግለጫው ይፋ አድርጓል።

LEAVE A REPLY