ከኦሮሚያ ክልል ለመጡ የመንግሥት ሠራተኞች ኮንዶሚኒየም እየተሰጠ ነው መባሉን የአ/አ መስተዳደር አስተባበለ

ከኦሮሚያ ክልል ለመጡ የመንግሥት ሠራተኞች ኮንዶሚኒየም እየተሰጠ ነው መባሉን የአ/አ መስተዳደር አስተባበለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየሰጠ ነው በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍፁም ከእውነት የራቀ ነው ሲል ገለጸ።

ሰሞኑን በተለይም በትናንትናው ዕለት እና ዛሬ በማኅበራዊ ድኅረ ገጾች ላይ ከተለያዮ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ለመጡ የመንግሥት ሠራተኞችና የኦሮሞ ብሔረሰብ አባላት የኮንዶሚኒየም ቤት እየታደለ ነው የሚሉ ጽሑፎች ሲስተናገዱ ነበር።
ይሁን እንጂ የታከለ ኡማ አስተዳደር ዛሬ ከሰዐት በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ መንግሥት እያስገነባቸው የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው ለሚገኙ ነዋሪዎች እንጂ ለተለያዩ ክልል ሠራተኞችም ይሁን ግለሰቦች የሚሰጥበት አሠራር የለውም ብሏል።
በ13ኛው ዙር እጣ የወጣላቸውና የወሰን ችግር የሌለባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለነዋሪዎች እየተላለፉ መሆኑን፣ ከትናንት በስትያ ጀምሮ የቁልፍ ርክክብ እየተካሄደ እንደሚገኝና በሁለት ሳምንት ውስጥም የቁልፍ ርክክብ የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልጿል።
“ከዚህ ውጪ በየትኛውም መንገድ የእጣ ማውጣት ሂደት የተከናወነ አለመሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።” ያለው መግለጫ፤ የከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እየሰጠ ነው በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ፍጹም የተሳሳተ እንደሆነ ሕዝብ ይወቅልኝ ማለቱን ሰምተናል።

LEAVE A REPLY