ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የዓለም ሕዝብ ተስፋ ያደረገበትና በሙከራ ላይ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ክትባት በዩናይትድ ኪንግደም በጎ ፈቃደኞች ላይ እየተሞከረ ነው ተባለ።
በቀጣይ ቀናት ውስጥ ለ300 ሰዎች ላይ ይሰጣል የተባለውን ክትባት የሚመሩት ከኢምፔሪያል ኮሌጅ ሎንዶን ፕሮፌሰር ሮቢን ሻቶክ፤ ክትባቱ በሰዎች ላይ ከመሞከሩ በፊት በእንሰሳት ላይ ተሞክሮ አበረታች ውጤት ማሳየቱን፣ ክትባቱ ጉዳት እንደማያስከትልና ሰውነት የመከላከያ ሴሎችን እንዲያመርት እንደሚያነቃቃው በእንሰሳት ላይ በተደረገው ሙከራ መረጋገጡን ገልጸዋል።
በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች ከዚህ ሙከራ በፊት በሰው ላይ ክትባታቸውን እየሞከሩ ሲሆን፤ የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ክትባት ሙከራ እየተደረገ ያለው በመላው ዓለም እንደሆነና በዓለም ዙሪያ በትንሹ 120 የክትባት ሙከራዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸው ተሰምቷል።
ከአፍሪካ ይህ ሙከራ በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ በጎ ፈቃደኛ ሰዎች እየተወሰደ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ አሉ።
የኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ክትባት ዛሬ በዩናይትድ ኪንግደም ሲጀመር የ39 ዓመቷ የፋይናንስ ባለሞያ ካቲ ከመጀመሪያዎቹ በጎ ፈቃደኞች አንዷ ሆና ተመዝግባለች።
“ተህዋሱን ለመዋጋት የእኔን ሚና መጫወት ስለፈለግኹ ነው” በማለት የበጎ ፍቃደኝነቷን መንስዔ የምትገልጸው ወጣቷ፤ በዚህ ረገድ የእኔ ሚና ምን መሆን እንዳለበት አላውቅም ነበር፤ ይህ አጋጣሚ ሲፈጠር ፈቃደኛ ለመሆን አላቅማማሁም ስትልም ተናግራለች።
በዚህ የመጀመሪያ ዙር ሙከራ የሚታዩ ውጤቶች ከተመዘገቡ በኋላ በሚቀጥለው ጥቅምት ክትባቱ ሌሎች 6ሺኅ ሰዎችን እንዲያሳትፍ ተደርጎ ይሞከራል ያሉት ባለሙያዎች፤ ክትባቱ ስኬታማ ከሆነ በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ በመላው ዓለም መሰራጨት ይጀመራል ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በመላው ዓለም 120 ቤተሙከራዎች ክትባት ለማግኘት እየሠሩ ቢሆንም ከእነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ከቤተ ሙከራ አልወጡም። በክሊኒካል ሙከራ ደረጃ የሚገኙት 13 ብቻ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ውስጥ 5ቱ በቻይና፣ 3 በአሜሪካ፣ 2 በዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁም በጀርመን፣ በአውስትራሊያና በሩሲያ አንድ አንድ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።