የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ተመሰረተ፤  ገለልተኝነቱ አጠያያቂ ሆኗል 

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ተመሰረተ፤  ገለልተኝነቱ አጠያያቂ ሆኗል 

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በኢትዮጵያዊያን የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ተነሳሽነት የተጀመረ ነው የተባለለት ማኅበር  ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ መመስረቱ ተነገረ።

በአገር ውስጥ እና ዓለም  ዐቀፍ የመገናኛ  ብዙኃን ድርጅቶች ባልደረቦች አባልነት የተቋቋመው ማኅበሩ ዛሬ ሰኔ 18/2012 ምስረታውን በሚመለከት መግለጫ ሰጥቷል።
በመገናኛ ብዙኃን ሙያና ሙያተኞች ላይ የተለያዩ አካላት በተለያየ መልኩ የሚደረገውን ተፅዕኖ እና ጫና ለማስቀረት፣ ለባለሙያው መብት እና ጥቅም የሚቆም፣ ሙያዊ ብቃቱን የሚያሳድግለት እና የኔ የሚለው የሙያ ማኅበራት ጥቂት በመሆናቸው እንዲሁም በአመርቂ ሁኔታ ለሙያተኛው ጥቅም እየሠሩ ባለመሆኑ፣ ይህ የመገናኛ ባለሙያዎች ማኅበር በመገናኛ ብዙኃን እና በሙያተኞች መካከል ትብብር እና አብሮ የመሥራትን መንፈስን ለመፍጠር ታቅዶ መመስረቱ ነው የተገለጸወ።
ማህበሩ ከሲቪክ ማህበራት ማደራጃ ኤጀንሲ ህጋዊ እውቅናን አግኝቶ የተመሰረተ መሆኑም በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተነግሯል።
ከዚህ ቀደም በተከናወነው የመስራቾች ጉባኤ ላይ የማህበሩን መመስረት አስፈላጊነት፣ ስያሜውን እንዲሁም አላማዎቹ ላይ በመወያየት የማኅበሩን አደረጃጀት በማፅደቅና ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ አባላትን በመምረጥ እና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ በማርቀቅ ወደስራ መግባቱን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት አስታውቋል።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች በተለይም የነፃው ፕሬስ አባላት አሁን ተመሰረተ የተባለውን ማኅበርና አደራጆቹን በተመለከተ ቅሬታ እንዳላቸው ይናገራሉ። ማኅበሩ ቀጥተኛ የሆነ የመንግሥት ድጋፍ የሚደረግለትና ገለልተኛ ሆኖ መቋቋም ያልቻለ ነው ሲሉም ይተቹታል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የሲቪክ ማኅበርነት እንዲያገኝ የተደረገው መስራቾቹ ከመንግስት ጋር ባላቸው ግንኙነት አንፃር እንደሆነ በማስረጃነት በማቅረብ የሚከራከሩት የኢትዮጵያ ነገ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነባር ጋዜጠኞች ከወራት በፊት የተመረጡት የማኅበሩ ዘጠኝ ሥራ አስፈጻሚዎች ውስጥ “የኢሕአዴግ ልሳን ” በመባል የሚታወቁት የኢቲቪ ጋዜጠኛ የነበረው ፍትህአወቅ ወንደሰንና ታናሽ ወንድሙ በአመራርነትና በመስራችነት መካተታቸው የማኅበሩን ገለልተኛነት እንድንጠራጠር አድርጎናል ብለዋል።

LEAVE A REPLY