በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ አልሆኑም

በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ አልሆኑም

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የፌዴራል የስነ ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ሥር ያለው የሃብት ማሳወቅ እና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት የመንግሥት ባለሥልጣናት የሀብት ምዝገባን እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።

የፌዴራል እና የክልል የስነ ምግባር እና የጸረ- ሙስና ኮሚሽኖች ማቋቋሚያ እና የሀብት ምዝገባ አዋጅ ፤ ከአፋር እና ከሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት በስተቀር በአዋጁ መሰረት የሀብት ማሳወቅ እና ምዝገባ ሂደቱ እንደሚካሄድ ማረጋገጫ ሰጥቷል።
የሀብት ምዝገባ ታማኝነት እና ግለጸኝነትን የሚያሳይ በመሆኑ፣ እያንዳንዱ የመንግሥት ተሿሚ ህጋዊ በሆነ መልኩ ሀብት የማፍራት መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ምዝገባ ማካሄዱ ለግለሰቡም ጭምር ጠቃሚ ነው ሲሉ የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይነህ ተናግረዋል።
በ2012 በጀት ዓመት በሀገር ዐቀፍ ደረጃ የ84 ሺኅ 460 ሀብት አስመዝጋቢዎችን መረጃ ለመመዝገብ ታቅዶ የ47ሺህ 184 ሀብት አስመዝጋቢዎችን መረጃ መመዝገብ መቻሉም ተሰምቷል። ምዝገባው የመንግሥት ተሿሚዎችን፣ የሕዝብ ተመራጮችን እና ምዝገባው የሚመለከታቸው የመንግሥት ሠራተኞችን ያካተተ እንደሆነም ታውቋል።
 የሀብት ማስመዝገቡ ሂደት በተፈለገው ልክ አለመሳካቱን የገለጹት አቶ መስፍን ይህ የሆነው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ተግባሩን በቁርጠኝነት ያልመሩት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
እያንዳንዱ የመንግሥት ተሿሚ እና ሀብት ማስመዝገብ የሚመለከተው ሁሉ፤ ግብር መክፈል ግዴታ እንደሆነው ሀብት ማስመዝገብንም እንደ ግዴታ በመቁጠር ሓላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉም ሓላፊው ሀብታቸውን ለማስመዝገብ አፈንግጠዋል የተባሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን አሳስበዋል።
በመመሪያው መሠረት እስከ ሰኔ 30፣ 2012 ዓ.ም ሁሉም የመንግሥት ተሿሚዎች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ በተደረገው ጥሪ ምዝገባው  በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው ያሉት አቶ መስፍን፤ ብዙ የሚቀሩ አካላት ግን እንዳሉና እነዚህ ግለሰቦች አሁንም እስከ ሰኔ 30 ድረስ ሀብታቸውን አስመዝግበው ማጠናቀቅ እንዳለባቸው አስረድተዋል።
ከሰኔ 30 በኋላ ግን ኮሚሽኑ እርምጃ እንደሚወስድ፣ ሀብት ያላስመዘገቡ ግለሰቦችን ከእነ ስማቸው እና ተቋማቸው ጭምር  ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ዛሬ በሰጠው መግለጫ ላይ ሰምተናል።

LEAVE A REPLY