ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የቻይናዊያን መኖሪያ ቤት ላይ የዘረፋ ወንጀል ፈጽመው ሊያመልጡ ከነበሩ ተጠርጣሪዎች መካከል ከፖሊስ ጋር በከፈቱት ተኩስ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ተሰማ።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አንድ የቻይናዊያን መኖሪያ ቤት ላይ የዘረፋ ወንጀል ፈጽመው ለማምለጥ የሞከሩት ሠባት ግለሰቦች ከፖሊስ ጋር በከፈቱት ተኩስ ሞትና ጉዳት ደርሷል።
ተጠረጣሪዎቹ በፖሊስ የክትትል አባላት ክትትል
እየተደረገባቸው ሳለ ወደ ቻይናውያኑ ቅጥር ጊቢ እንደገቡና ዘረፋውን ፈጽመው ሲወጡ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ቢጠየቁም አሻፈረኝ ብለው ተኩስ በመክፈታቸው፤ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሂደት ሊያመልጡ ከሞከሩ ሁለት ግለሰቦች አንዱ ህይወቱ ሲያልፍ፣ ሌላኛው ቆሰሎ ለህክምና ወደ ሆስፒታል መወሰዱን ከደረሰን መረጃ መረዳት ችለናል።
ቀሪዎቹ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ መሆኑን የጠቆሙት ምንጮች፤ ግለሰቦቹ ቀደም ሲልም የተለያዩ የጸጥታ አካላትን የደንብ ልብሶች በመልበስ እና የጦር መሳሪያ በመታጠቅ፣ እንዲሁም የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም በተለያዩ ሥፍራዎች የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ለመቆየታቸው ከሕዝብ ጥቆማ እንደተሰጠም ተናግረዋል።