ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሶልማክ አድቨርታይዚንግ ኤንድ ኤቨንትስ፤ ከኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ሙዚቀኞች ህብረት ጋር በመሆን ባካሄደው የጎዳና ላይ የሙዚቃ ዝግጅት ከ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናገረ።
ዝግጅቱ በአይነቱ ለየት ያለ እና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዕለት ገቢያቸው ተጓድ፣ በከፋ ችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት የታሰበ ነው።
በተለምዶ ቦሌ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ዝግጅት መርሃ ግብር ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይነት እና የቁሳቁስ ድጋፍ መሰብሰብ መቻሉ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች አረጋግጠዋል።
የሶል ማክ አድቨርታይዚንግ ኤንድ ኤቨንትስ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ሰለሞን መኮንን የሙዚቃ ኮንሰርቱ የተዘጋጀው በኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ሙዚቀኞችን በማሰባሰብ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እና ከማህበራዊ ትረስት ፈንድ ኤጀንሲ በተገኘ ፍቃድና ትብብር እንደሆነ ገልጿል።
ለሁለት ቀናት፣ ቅዳሜ ሰኔ13 እና እሁድ ሰኔ 14/2012 ዓ.ም በተካሄዱት የገቢ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የአይነት እና የቁሳቁስ ድጋፍ ተሰብስቦ ለ250 አባወራዎች ድጋፉ መከፋፈሉን ያመላከቱት አዘጋጆቹ፤ ይህ ድጋፍ ለማድረግ ከታሰበው የበለጠ እንደሆነ ነው ብለዋል።
በዚህ የሙዚቃ ኮንሰርት ከ100 በላይ የሚሆኑ የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋቾች እና ሙዚቀኞች የተሳተፉበት ሲሆን የተለያዩ ዓይነት የሙዚቃ መሳሪያዎችን እና ለዝግጅቱ ግብዓት በመሆን የሚገለግሉ ቁሳቁሶችን ከክፍያ ነጻ በማበርከት ቴክ ፋይፍ የሙዚቃ መሳሪያ አስመጪ እና ሽያጭ ፣ እንዲሁም ነብዩ እና እንየው ፈጣን ምግቦች የሽርክና ማኅበር ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸው ተሰምቷል።