ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ለጉምሩክ ኮሚሽን ሠራተኞች ብር 200 ሺኅ ብሮ ጉቦ በመስጠት ንግድ ለማጭበርበር የሞከረ ባለሀብት በተቋሙ ሠራተኞች አጋላጭነት እጅ ከፍንጅ መያዙ ተነገረ።
“ያዴሳ ደሬሳ ጀነራል ትሬዲንግ ” ስም በዲክላራሲዮን ቁጥር 8-147/20 በቀን 11/01/20 የተመዘገበ ሀገር አቋራጭ ትራንዚት ዕቃ ፤ ለእቃው ዋስትና ብር 4,370,000 በማሲያዝ በመተሀር ቡርቤ አድርጎ ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲጓጓዝ፣ በ31/01/2020 የትራንዚት ፈቃድ ተሰጥቶት ነበር።
ይሁን እንጂ ከሀገር ይወጣሉ ተብለው በትራንዚት ላይ የነበረ በ2 ተሽከርካሪዎች የተጫነ ዕቃ ሳይወጣ የቀረ፣ እንዲሁም አስመጪው በህገ ወጥ መንገድ እቃው ሳይወጣ እንደወጣ በማስመሰል ማረጋገጫ እንዲጻፍለት ሙከራ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከእንዲህ ዓይነቱ ህገ ወጥ አፈፃፀም ጋር በተያያዘ መረጃው ለኮሚሽኑ አመራር የደረሰ በመሆኑ ክትትል ሲደረግ ቆይቶ፤ ትናንት በቀን 20/10/2012 ዓ.ም የዕቃው ባለቤት ያሲያዘዉ ዋስትና ብር 4,370,000 (አራት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ ብር) እንዲመለስለት፣ በተጨማሪም ዕቃው ከሀገር ሳይወጣ እንደወጣ በማድረግ ማረጋገጫ ለማግኘት ሙከራ ሲያደርግ ጉዳዮን ሲከታተሉ በነበሩ የኮሚሽኑ ኢንተሊጀንስ ባለሙያዎች ግለሰቡ ጉቦ ለመስጠት ሲሞክር እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ግለሰቡ ከያዘው ብር 200 ሺኅ ጋር የጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ወንጀል ምርመራ ዲቪዢን ጋር በመተባበር ግለሰቡንና ተባባሪ ግብረአበር የሆነውን አቶ አብዱልቃዲር ዘይኑ ሃሽምን ቦሌ ዓለም ሲኒማ አካባቢ በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው የገቢዎች ሚኒስቴር አስታውቋል።