ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኢራን መንግሥት በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱ ተነገረ።
የአረብ ሀገራት ቅርብ ሚዲያ እንደሆነ የሚነገርለት አልጀዚራ በሰበር ዜናው ፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ ኢራን ትዕዛዝ ማውጣቷን ይፋ አድርጓል።
የእስር ማዘዣው በፕሬዝዳንቱ ላይ ለመውጣቱ ምክንያት ከወራት በፊት የኢራኑ ጀነራል ቃሴም ሶሌማኒ ኢራቅ ውስጥ በትራምፕ ትእዛዝ፣ በድሮን አማካኝነት በተፈፀመ ጥቃት መገደላቸው እንደሆነም ተነግሯል።
ይህ ጥቃት ከደረሰ ከዐራት ቀናት በኋላ ፣ ቴህራን በአሜሪካ ወታደሮች በሚተዳደሩ ሁለት የኢራን ማዕከላት የተኩስ ጥቃትን በመሰንዘር የበቀል እርምጃ ማድረጓ አይዘነጋም።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ የተባበሩት መንግሥታት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በኢራን ላይ እንዲያራዘም ግፊት እንድታደርግ ሲወተውቱ ሰንብተዋል።
ዛሬ ይፋ የሆነው ዘገባ እንደሚያስረዳው ከሆነ ዶናልድ ትራምፕንና በወቅቱ በጀነራሉ ግድያ የተሳተፉ ከ30 የሚልቁ ሰዎችን አድኖ እንዲያቀርብላቸው የኢራን ባለስልጣናት ኢንተርፖልን መጠየቃቸውም ከዘገባው ለማወቅ ተችሏል።