ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የህዳሴው ግድብ በደለል እንዳይሞላ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ገለጹ።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች በሱሉልታ ወረዳ ደርባ ከተማ አካባቢ ዛሬ ከ27 ሺኅ 700 በላይ ችግኞችን መትከላቸው ተነግሯል።
“ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን ከራሷ አልፎ ለተፋሰሱ ሀገራትም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው” ሲሉ በችግኝ ተከላው ላይ የተናገሩት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ፤ ችግኞችን መትከል አካባቢን ከመራቆት መከላከል ባሻገር ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ዘለቄታዊ ዋስትና አለው ሲሉም ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በዋናነት ለራሷ እንደምትሠራ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በተጨማሪም የተፋሰሱ ሀገራት ውኃ እንዲያገኙ ያስችላል ከማለታቸው ባሻገር፣
የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ሥራ የአፈር መሸርሸርን ስለሚያስቀር የተፋሰሱ ሀገራት ፕሮጀክቶችም በደለል እንዳይሞሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብረሃ አዱኛ በበኩላቸው የሕዳሴ ግድቡ የሁሉም አሻራ ያረፈበት በመሆኑ ከወዲሁ ልንከባከበው ይገባል ብለዋል።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው እየተለወጠ የመጣውን የዓለማችንን የአየር ጠባይ ለማስተካከል የአካባቢ ጥበቃ ወሳኝ ነው ካሉ በኋላ፣ ችግኞችን መትከል ብቻ ሣይሆን በመንከባከብ እንዲጸድቁ ማድረግም ይገባል ሲሉም ምክር ለግሰዋል።
የብሔራዊ ሚትሮዎሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክትር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው፣ እየተለዋወጠ የመጣውን የአየር ጠባይ ለማስተካከል ችግኝ መትክል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት በ115 የችግኝ ጣቢያዎች ከ100 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ያዘጋጁ ሲሆን ፤ ሁሉም በዚህ ዓመት ይተከላሉ ሲል አስታውቋል።