ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሕጻናት ላይ የአስገድዶ መድፈር የሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ የሚተላለፈው የፍርድ ውሳኔ ዝቅተኛ መሆኑ ወንጀሉን በከፍተኛ ሁኔታ ከማባባሱ ባሻገር በኅብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታን እየፈጠረ ይገኛል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ከተማ የ10 ዓመት ህጻን ልጁን የደፈረው የፖሊስ አባል በ9 ዓመት ጽኑ እስራት ብቻ መቀጣቱ በዚህ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያንን እያነጋገረ መሆኑን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተመልክተናል።
የካማሽ ዞን ማረሚያ ቤት የሥራ ባልደረባ የሆነው ዋ/ሳጅን በላይ ታየ የገዛ ልጁን የ10 ዓመት ሕጻን አስገድዶ የደፈራት መሆኑን የካማሽ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አቤቱታ መቀበል መመርመር ዋና ሥራ ሂደት ባለቤት ዋና ኢንስፔክተር ቃበታ ማረጋገጫ መስጠታቸው የፍርድ ውሳኔው ሲሰማ ከፍተኛ ግርምትን እንዲፈጠር አድርጓል።
ነዋሪነቱ ካማሽ ከተማ 02 ቀበሌ የሆነው ግለሰብ ታህሳስ 08/04/2012 ዓ/ም በግምት ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ፣ የሕጻኗ እናት ቤተሰብ ሞቶባት ለሃዘን በመሄዷ፣ ከመጠን በላይ ጠጥቶ ሰክሮ በመምጣት በቤት ውስጥ የነበረችውን የ10 ዓመቷን ሕጻን ልጁን ከደበደባት በኋላ አስገድዶ የደፈራት መሆኑ በምርመራ ተረጋግጧል።
የካማሽ ወረዳ ፍ/ቤትም የቀረበለትን ክስ ሲመረምር ከቆየ በኋላ ግለሰቡ የመከላከል መብቱ ተጠብቆለት መከላከል ባለመቻሉ የዐቃቢ ህግን ማስረጃ በመንተራስ ፍ/ቤቱ በ17/10/2012 ዓ/ም በዋለው የወንጀል ችሎት ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑ በመረጋገጡ በ9 /ዘጠኝ/ ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፖሊስ ኮሚሽን ቢገልጽም በጨቅላዋ ላይ ከደረሰው ጥቃት፣ ግለሰቡም የህግ ሰው ከመሆኑ አኳያ ፍርዱ አነስተኛ እንደሆነ ብዙዎች በመናገር ላይ ናቸው።