ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ከፌደራል መንግሥቱ ሙሉ ለሙሉ ያፈነገጠው ህወሓት ራሱ ያወጣውን ሕገ መንግሥት የሚጣረሱ ድርጊቶች መፈጸሙን ገፍቶበታል።

መቀሌ በመሸገው ወንጀለኛ ቡድን እንደሚዘወር የሚነገርለት የትግራይ ክልል የራሱን የምርጫ ኮሚሽን ለማቋቋም የሚያስችለው አዋጅ ፤ እንዲሁም የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ አዘጋጅቶ ለውይይት ማቅረቡ ተሰማ።
በኢትዮጵያ በወርሃ ነሐሴ ምርጫ  ሊካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ምርጫው ወደ ሌላ ጊዜ እንዲዘዋወር መወሰኑ ይታወቃል። ይሁን እንጂ  የትግራይ ክልል  ስድስተኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ እንደወሰነ ደጋግሞ እየገለጸ ይገኛል።
ህወሓት በክልሉ ለማካሄድ ዕቅድ ከያዘለት ክልላዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ባዘጋጃቸው ሁለት የሕግ ረቂቅ ሰነዶች ላይ  ነገ (ማክሰኞ) በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለመወየያያት ቀጠሮ መያዙ ተሰምቷል።
ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ከሚደረግባቸው ረቂቅ ሰነዶች አንዱ የምርጫና የምርጫ ሥነምግባር ረቂቅ አዋጁ 130 አንቀጾችን የያዘ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል። ሁለተኛው ሰነድ  የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የምርጫ ኮሚሽን ለማቋቋም ለማደራጀት፣ እንዲሁም ሥልጣኑንና ተግባሩን ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ እንደሆነም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ነገ የህወሓት ደጋፊ የሆኑና ከፓርቲው ድጎማ የሚደረግላቸውና ቀለብ የሚሰፈርላቸው ጥቂት ተለጣፊ የትግራይ ፓርቲዎች በተገኙበት ነገ ውይይት ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው አዋጅ 33 አንቀጾችን የያዘና 27 ገጾች ያሉት ሰነድ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።።
ምርጫው ወደ 2013 ዓ.ም ሲራዘም ተቃውሟቸውን ካሰሙ አካላት መካከል አንዱ የሆነው የትግራይ ክልል ወቅቱን ጠብቆ ምርጫውን ለማካሄድ የገፋበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ የፌደራል መንግሥቱ ምን ዓይነት እርምጃ ይወስዳል የሚለው በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የክልሉን ጥያቄ ውድቅ ካደረገ በኋላ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትግራይ ክልል ለማካሄድ የጠየቀውን የክልላዊ ምርጫ ለማስፈጸም የሚያስችለው ሁኔታ የለም ማለቱም የሚዘነጋ አይደለም።

LEAVE A REPLY