ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ክልሎች
ተወልጄ ያደግኩት አርሲ ነገሌ፤ ነገሌ አርሲ ነው፡፡ይሄንን ነገር ለመጻፍና ላለመጻፍ ከራሴም ከሰውምተሟግቻለሁ፡፡ ባንድ በኩል ነገር ማባባስ መሰለኝ፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ንጹሀን ደማቸው ደመከልብሲሆን ዝም ማለት ተባባሪነት ወይም ግዴለሽነትሆነብኝ፡፡ በሁለት አስጨናቂ ጥያቄዎች ተፋጠጥኩ፡፡የማከብረው ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ፤ “ልጅ ወንድወሰንይሄንን ባትጽፍ ነው ስህተቱ፡“ አለኝ፡፡ ቢያንስሳንጨማመር እውነቱን ብንጽፍ ግን የሚመለከታቸውሁሉ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ይሄ የተጻፈው፤ለማስተማሪያ ነው፡፡ ለቂም በቀል አይደለም፡፡ ለጊዜውተበቃይ አላህ/እግዚአብሄር ነው፡፡
ፍጹም ባረገው አብሮ አደጋችን ነው፡፡ ለፍቶ፤ ጥሮ ግሮያደገ ልጅ ነው፡፡ ደግ፤ ርህሩህ ነው፡፡ በመጨረሻምደግነቱ አስገደለው፡፡ ማክሰኞ፤ ሰኔ 23 ቀን፤የተወለደበት፤ እትብቱ የተቀበረበት ከተማ በአሰቃቂሁኔታ ተገደለ፡፡ የደሜን አስከሬን ለማዳን ብሎ፡፡ ደሜ፤ጎንደሬ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ለአመታት አረቄ ነግዶባፈራው ሀብት ነው ቢዝነሱን የገነባው፡፡ አለምምግብ ቤት፡፡ ቢዝነሱ፤ በአመጸኞች ባንድ ቀንወደመ፡፡ ንብረቱ ጦሱን ይዞ ቢሄድ ጥሩ ነበር፡፡አልሆነም፡፡ የሱንም የወንድሙንም ሕይወት በአሰቃቂሁኔታ ቀጠፉት፡፡ በገጀራና በመጥረቢያ ከትክተው፡፡የደሜን አስከሬን ምድር ለምድር ሲጎትቱ ሲመለከት፤አብሮአደጋችን ፍጹም ባረገው “ተዉ እንጂ፤ገደላችሁት ምናለ አሁን አስከሬኑን እንኳንብትተዉት“ ብሎ ጠየቀ፡፡ በመጥረቢያ ጭንቅላቱንብለው የገደሉት፡፡
ቤተሰብ ከመፍራቱ የተነሳ፤ የልጃቸውን ግድያ በአጥር፤በቀዳዳ አጮልቆ ከመመልከት ውጪ ምንም ማድረግአልቻሉም፡፡ ወደኋላ ላይ፤ የነጌሌ ጎረቤት ከተሞች፤አባወራዎች፤ ሚስቶቻቸውንና ልጆቸውን ጥለውሲሸሹና ከኋላቸው ሲገደሉ እንመለከታለን፡፡ለወትሮው፤ በጦርነት ሰዓት እንኳን፤ ሴትና ሕጻንአይገደልማ፡፡ የኦሮሞም፤ የአማራም ባህል አይደለማ፡፡በነጌሌና በዙሪያዋ የሆነው ግን፤ ከባህልም፤ ከሕግም፤ከሀይማኖትም ያፈነገጠ ነው፡፡ የሩዋንዳ ቅምሻ፡፡
ፍጹም እሱን እንደማይነኩት እርግጠኛ ነበር፡፡ምክንያቱም የተወለደበት፤ ያደገበት፤ ቤተሰቦቹየገነቧት ከተማ ነቻ፤ ነጌሌ አርሲ፤ አርሲ ነጌሌ፡፡ይገድሉኛል አይደለም፤ ይቆጡኛል ብሎ አላሰበም፡፡እነሱ ግን፤ ስልጣኔ ያልጎበኛቸው አረመኔዎች ናቸው፡፡ገዳዮቹን ማለቴ ነው፡፡አይን የላቸውም፡፡ ከመካከላቸው አንዱ እጅ አያሳርፍ፡፡ ካሳረፈ፤ አበቃ፡፡ ሌሎቹ ሳያገናዝቡ፤ ሳይጠይቁ ይሰፍሩበታል፡፡ ይሄን የፈጸሙት፤ ከተማው ውስጥ ታይተው የማታወቁ ባእዶች ናቸው፡፡ይሄን ኦሮሞ አይፈጽምም፡፡ እነዚህ ኦሮሞዎችአይደሉም፡፡ በምግባራቸው፤ በፈቃዳቸው ከኦሮሞነትተገንጥለው ወጥተዋል፡፡ ስለዚህ ፍጹምን ገደሉት፡፡መግደልም ብቻ አይደለም፤ እንደሰማሁት ከሆነአስከሬኑን በገመድ ጎተቱት፤ ስልክ እንጨት ላይም ሊያንጠለጥሉት ታገሉ፡፡ ይሄ ሁሉ የተከሰተው ነጌሌአርሲ ነው፡፡ የቀድሞው ምስራቅ ሸዋ ዞን፤ ምእራብአርሲ ተብሏል አሁን፡፡
አስጨናቂ፤ ከሰውነት ጎዳና ወጥቶ፤ አተላ አገላብጦከብት ቀልቦ፤ እንደምንም ተሟሙቶ ቢዝነስ ከፈተ፡፡ ድርጅቱን እንዳለ አቃጠሉበት፡፡ አባቱንም ከአመታት በፊት በዚህ ሁኔታ እንደገደሉበት ሰምቻለሁ፡፡ እነሆነገሌ፤ ረቡእ ሰኔ 25 በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ 4 ሰዎች ቀበረች፡፡ ከተማው አዘነ፡፡ እንደራሄል እንባውን ረጨ፡፡ መጽናናትን ግን አላገኘም፡፡ የሚያጽናናው መንግስት፤ የሚተማመንብት ሕግ የለም፡፡ የክልሉም፤ የፌደራሉም ሕገ-መንግስቶች እንደጉድ ተጣሱ፡፡ መጽሀፍ ቅዱስና ቅዱስ ቁርአን ተጣሰ፡፡ የሰማዩም የምድሩም ሕግ ከተጣሰ፤ ሰው በምን ይጽናናል?
ንብረታቸው የተቃጠለው የትየለሌ ናቸው፡፡ ይሄ በነጌሌብቻ የተከሰተው ነው፡፡ በጎረቤት ከተሞች የተከሰተውግድያ እጥፍ ነው፡፡ ለምሳሌ፤ አንድ አብሮአደጌ የነገረኝ ታሪክ እንዲህ ነው፡፡ የነጌለሌው መንግስቱ ቀጸላ፤ ኢትዮጵያን ከ30 ዓመት በላይ ያገለገሉ ቆፍጣና ወታደር ነበሩ፡፡ ትንሽዋ ልጃቸው ጸሀይ መንግሰቱ ከባሏና ከሁለት ልጆቿ ጋር አዳሚቱሉ ላይ የግብርና ቢዝነስ ከፍታ፣ መኖሪያቸውን ደግሞ ዘዋይ አድርገው ይኖሩ ነበር፡፡ እሷንም፤ ባሏንም፤ ልጆቿንም፣ የዘመድ ልጅም ገደሏቸው፡፡ አረዷቸው፡፡ ሊትራሊ፤ አረዷቸው፡፡ የ31 አመተቱ ሳሙኤል፣ የ28 አመቷ ነፃነትታረዱ። በ20ዎቹ ውስጥ የሚገኘው የአጎት ልጃቸው፤ ዋሲሁን ታረደ። አዳሚ ቱሉ የሚገኙ 4 ቤተሰቦቻቸው ለጊዜው ተርፈዋል። ሌላ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች በጎረቤት ከተሞች/መንደሮች ታርደዋል፡፡ ስማቸውንና ዝርዝራቸው እንደደረሰን እናቀርባለን፡፡
እነዚህ ማክሰኞ እለት የተገደሉ፤ ጋዝ አርከፍክፈው ንብረታቸው የወደመ ሰዎች ካንድ ብሄር ብቻ አልመጡም፡፡ መምህር ፈቃደ ደጀኔ፤ እናቱ ኦሮሞ ናቸው፡፡ ትውልድ አንጻለው ብሎ የገነባቸውን ትምህርት ቤቶቹን አወደሟቸው፡፡ ትምህርት ቤቱን ከአመት በፊት ጀምረውት ነበር፡፡ አሁን ጨረሱት፡፡አዲስ አበባ መሆኑ በጀው እንጂ፤ እሱም አይቀርለትም ነበር፡፡ በጦርነት ሰዓት እንኳን፤ ትምህርትቤቶች፤ ሆስፒታሎች፤ የጦር ኢላማ አይደሉም፡፡
እነዚህ ሰዎች የመጡት፤ ክርስቲያኑ ላይ ብቻም አይደሉም፡፡ መንሱር፤ ሌላ አብሮአደጋችን ነው፡፡ እሱም እህቶቹም/ወንድሞቹ አንድ ትምህርት ቤት ተምረናል፡፡ እኛ ጠላ ቤት ስናውደልድል፤ መንሱር ከልጅነቱ ጀምሮ ወጥሮ ሰርቶ ያደገ ሙስሊም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ንብረቱን አቃጠሉት፡፡ ይሄ ግድያ በዛ፡፡ በጣም በዛ፡፡ በተለይ ነጌሌን ደጋገማት፡፡ እንዴት ኦሮሞን፤ የአርሲንብሄር በማይወክሉ፤ በጥቂቶች፤ እንሰቃያለን? ምክንያቱም ክልሉ ለአቅመ ክልልነት አልደረሰም፡፡ ሰው ክልል ከሆነ፤ መንግስት ከሆነ በኋላ፤ እንዴት እንደአውሬ ይሰራል?
እንደሰማሁት ከሆነ፤ የቆዩት የከተማው ነጋዴዎች፤ እነአቶ ትግስቱ፤ እነ አቶ ተስፋየ ዲልቦ፤ ሌሎችም ቢዝነስ ባለቤቶች በሚደርስባቸው ጥቃት፤ ግፍ አዝነው፤ ተስፋ ቆርጠው፤ ከከተማው ነቅለው ለመውጣት መንገድ ጀምረው ነበር፡፡ ደግሞ ደጋግሞ የራሱን ክልል/ዞን/ወረዳ የሚያቃጥል የ29 አመታት ድንቁርና ትምህርት የሰራበት ባእድ ትውልድ ተመልሶ መጥቶን ብረታቸውን ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸው እንደሚነጥቃቸው አውቀውታል፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ ነጋዴዎች ወደአዲስ አበባ፤ ወይም ወደሌሎች ጎረቤት አገሮች ገብተዋል፡፡ እነትግስቱን ግን፤ የአገር ሽማግሌዎች ለምነዋቸው፤ “እንዴት ሆኖ የገነባችሁትን፤ ለወግ ለማእረግ የበቃችሁበትን ከተማጥላችሁ ትሄዳላችሁ“ ተብለው፤ ተለምነው ነውሀሳባቸውን ለውጠው የቀሩት፡፡ ዛሬ መንግስት አላዳናቸውም፡፡ የአቶ ትግስቱ የተቃጠሉት ሻሸመኔም ነጌሌም ያሉት ቢዝነሶቹ ብቻ አይደሉም፡፡ በዚህ ዙርመኖሪያ ቤቱም ጭምር እንጂ፡፡ ጉራጌ ጎበዝ ነው፡፡ንብረቱን ሰርቶ ያገኘዋል፡፡ አፈር ልሶ ይነሳል፡፡ 29 አመትእንደጉራጌ የተቀጠቀጠ ማን አለ? ሕይወቱን ግንበምን ይተካዋል? እንደሰማሁት ከሆነ፤ አቶ ትግስቱዛሬም በሕይወት አምልጧል፡፡
የሚገርመው፤ የሚያሳዝነው የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ስራነው፡፡ ከሀጫሉ ግድያ ቀደም ብሎ በነበሩት ቀናት፤ ኮቪድ19 ከመጣ በኋላ በከተማው የሰፈሩት ልዩሀይሎች፤ የከተማውን ህዝብ ቁም ስቅሉን አሳይተውት ነበር፡፡ ሰአት እላፊ ማታ 3 ሰዓት ሆኖ ሳለ፤ገና 1 ሰዓት ላይ መንገድ ላይ ያገኙትን ሁሉ ክፉኛ ይደበድቡ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ በድብደባው ክፉኛቆስለው ሆስፒታል የገቡም አሉ፡፡ ማስክ አላደረጋችሁም ብለው በቀን በብርሀን በአደባባይሰዉን ይቀጠቅጡ ነበር፡፡ አልፈው ሄደውም፤ ጸጉር አጎፈርክ ወይም ፍሪዝ አደረግክ ብለው በመቀስመቁረጥ ሁሉ ጀምረው ነበር፡፡ የሚያስሩት የሚያንገላቱት ዜጋ ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ ስለዚህም፤ ዘረኛ፤ ስርአት አልበኛ ጎረምሶች ከተማውን ወረውሰው ሲገድሉ፤ ቤት ንብረት፤ ቢዝነሶች ሲያቃጥሉ ልዩሀይል አልታይ አለ፡፡ ከታየም፤ ዝም ብሎ ይመለከታል፡፡ ሰዉን ለመከላከል ምንም ጥረት አላደረጉም፡፡ ማድረግ አይደለም፤ ሰዉም ተደራጅቶ ራሱን እንዳይከላከል ፈራ፡፡ እንደውም፤ ከአካባቢው እንደደረሰኝ መረጃከሆነ፤ ከተማው ሲቃጠል፤ ልዩ ሀይሎች ከካምፓቸው ሆነው፤ ቃጠሎው በደንብ እንዲታያቸው፤ ዛፍፍ ላይወጥተው ይመለከቱ ነበር፡፡ ልዩ ሀይልና መስተዳድሩ፤ የኦህዴድ/ብልጽግና ካድሬዎች፤ በደንብ ከተመረመረ፤ከጀርባ ሆነው ሳይገፋፉም አይቀርም፡፡
በዚህኛው ዙር ይህ ስለመደረጉ መረጃ የለኝም፡፡ቀደም ባሉት ጊዜያት ግን ተመሳሳይ ዘረፋዎችና ግድያዎች ሲከሰቱ፤ ሕዝቡ አሁንስ በዛ ብሎ ራሱን ለመከላከል ሞክሮ ነበር፡፡ የተወሰኑ አካባቢዎች ተሳካላቸው፡፡ የተወሰኑት ግን ጭራሹኑ በፖሊስተደበደቡ፡፡ ሕዝቡ ሲያይልና ዘራፊዎቹን ሲያባርር፤ፖሊስ ለዘራፊዎቹ ወግኖ ሕዝቡን ያንገላታል፡፡ ራስን ለመከላከል ጥይት ወደሰማይ የተኮሱ ሰዎች፤ ሰላም አደፈረሳችሁ ተብለው ታስረዋል፡፡ የልዩ ሀይልና የፖሊስ ችግር ሰዉን ከጥቃት አላማስጣላቸው ብቻ ሳይሆን፤ ሰዉ ራሱን ለመከላከል እንዳይደራጅ ማድረጋቸው ነው፡፡ በዚህ ወደዘር ማጥፋት ሙከራ ለሚጠጋድርጊት ፖሊስ/ልዩ ሀይል ተጠያቂ ነው፡፡ መንግስት ሕዝቡን ቢተወው፤ ራሱን በመከላከል ይሞታል፡፡ ከተማውን ከዝርፊያ ማስጣል አይደለም፤ ወፍ ዝርእንዳይል ማድረግ ይችላል፡፡ መንግስት አንደኛው ቡድንወደአውሬነት ሲለወጥ፤ ሌላኛውን ሕዝብ አስሮ ማስደብደብ ግን ግፍ ነው፡፡ የግፍ ግፍ፡፡ ወንጀል ነው፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ/ልዩ ሀይል ያደረገው ያንን ነው፡፡የሩዋንዳ ቅምሻ፡፡
ጥቃቱ ሕዝባዊ ወይም ብሄር-ለበስ አይደለም፡፡ማለትም፤ ይሄኛው ብሄር ያኛውን ብሄር አይደለም ያጠቃው፡፡ ጥቃቱ ግን በርግጠኝነት መዋቅራዊ ነው፡፡ ገዚው ፓርቲ ብልጽግናና እሱ የሚመራቸው፤ እሱ ያሰለጠናቸው ልዩ ሀይሎች ህዝቡን አላዳኑትም፡፡ወይም በቀጥታም ይሁን በዝምታ፤ ከነፍሰ ገዳዮቹ ጋርአብረዋል፡፡ እንጂ፤ የከተማው ኦሮሞም ፈርቶ ተደብቆነበር፡፡ የደፈረ ኦሮሞም ገላግሏል፡፡ አብሮ አልቅሷል፡፡ አብሮ አዝኗል፡፡ ሕዝብን ከጥቃት መጠበቅ ካልቻለ፤ ሀያ ሰላሳ ዙር ልዩ ሀይል ማሰልጠን ምን ዋጋ አለው? መንግስት failed us፡፡ በጣም failed us፡፡ ገዳዮቹ፤ ገድለው፤ ዘርፈው፤ አቃጥለው ሲደክማቸውና ሲመሽነው የሄዱት፡፡ መከላከያ ሲደርስ፤ ስራው አልቋል፡፡ ለጊዜው መከላከያ አረጋግቷል፡፡ ግን እስከመቼ?
ሕገ መንግስቱ ተናደ፡፡ አንቀጽ 25፤ የእኩልነት መብትድሮም የለም፡፡ የሕገመንግስቱ አንቀጽ 10፤ የዜጎችናየሕዝቦች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብትን ያጎናጸፈው አንቀጽ ግን ዛሬም ተናደ፡፡ ዴሞክራሲውይቅርብን፤ ሀይሌ ገብረስላሴ ከአመታት በፊትእንዳለው፤ ዴሞክራሲ፤ በመረጥነው፤ ባቋቋምነውመንግስት መተዳደር፤ ለኛ ቅንጦት ነው፡፡ ያንን ለመረዳት የሀይሌን ያህል መማር፤ የሀይሌን ያህልመሮጥ አያስፈልግም፡፡ ነገሌ ወይም አንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች/ዞኖች መኖር በቂ ነው፡፡ ሰብአዊነትግን እንዴት አጣን? ሀይማኖትስ የለንም? አንቀጽ 14፤ 15፤ 16 የሕይወትና የአካል ደህንነት መጠበቅ፤ አፈርድሜ ጋጠ፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ ችለነው እንጂ ዜግነትበህግ ሳይሆን፤ ዜግነት በደምና በቋንቋ ነው፡፡ ይሄ የኦሮሞም ባህል አይመስለኝም፡፡ ኦሮሞ እንደዚህ አይደለም፡፡ በኦሮሞ ስም የሚነግዱ ጸረ-ኦሮሞዎች እንጂ፡፡ ይሄ ከሀጫሉ ሞት ጋርም አይገናኝም፡፡ ቀድሞ ከተደበቀ፤ የቆየ መዋቅራዊ፤ መንግስታዊ/ድርጅታዊ ድጋፍ ያለው ጥላቻ እንጂ፡፡ እኛ የምናውቀው ኦሮሞይሄ አይደለም፡፡ ኦሮሞ ··· ፡፡ ይቀጥላል
ወንድወሰን ተሾመ || ኢጆሌ ነጌሌ-ከዲሲ፤ (ሰኔ 26,2012)
አቶ ወንድወሰን ተሾም፤ ይህንን ማስታውሻ በምጻፍህ ልትመሰገን ይገባል። ሆኖም አንድ የዘነጋኽው ጉድይ አለ። ይኽውም የህገ መንግሥቱ ጉዳይ ነው። ሐገራችንና ህዝቧን ዛሬ ያሉባት ቦታ ያደርስ ይኽው ዘረኛና ከፋፋይ ሕገ-መንግስት ነው። በዚህሕ ሕገ-መንግሥት እየተገዛን እስክቆየን ድረስ፤ ሁኔታው ተባብሶ ከዚህም የከፋ እንደሚሆን መጠራጠር አይቻልም። እንዳልከውም ሩዋንዳ ደርሶ መልስ ማድረጋችን ግልጽ ነው። አምላክ ደግሞ የሚሳነው ነገር ስለሌለ ከክፉ ይሰውረን ማለት።