ባለፈው ሰኞ አመሻሻቱ ላይ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በታጣቂዎች ህይወቱ የተቀጠፈው አክቲቪስት እና አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ አሟሟት በገለልተኛ ወገኖች እንዲጣራ ተጠየቀ፣ግድያውን ተከትሎ ውጥረት ነግሷል፣ የበርካታ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፣ እስራት ከአገር ቤት እስከ ባህር ማዶ የዘለቀ ተካሄዷል፣በርካታ ንብረት ወድሟል፣የኢንተር ኔት አገልግሎት ተቋርጧል።
ሲ ኤን ኤ እንደ ዘገበው ማክሰኞ እለት የተቀሰቀሰውን ያለመረጋጋትን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ደረሰ በተባለ የቦንብ ፍንዳታ ቦንቡን አጠመዱ የተባሉ ጨምሮቶ ፣የጀዋር መሀመድ ታጣቂዎችን ትጥቅ ለማስፈታት ከተጓዙ የጸጥታ ኃይሎች አንዱን ጨምሮ አስር የሚደርሱ ሰዎች ህይወታቸው የጠፋ ሲሆን ወደ ሰማኒያ የሚጠጉ ሰዎች ቆስለዋል።፣ የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ ስራ አስኪያጅ የሆነው ጀዋር መሀመድን እና አቶ በቀለ ግፕርባን ጨምሮ ወደ ሰላሳ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋለቸውን ፖሊስ አረጋግጣል።በግቢው ደጃፍ ተቃዋሚዎችን ያስተናገደው ፣የተኩስ ድምጽ መስማቱን የገለጸው በአዲስ አባባ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ባወጣው የደህንነት መግለጫው “ያልተረጋጋ ድባብ”ብሎታል።
ማክሰኞ ምሽት በቴሌቭዥን መስኮት አማካኝነት መግለጫ የሰጡት ጠ/ሚ/ር አብይ አህመድ ድርጊቱን” ሰይጣናዊ ፣ እድገታችንን በማይሹ በአገር ውስጥ እና በውጪ ኃይሎች የተቀነባበረ ድርጊት ነው”በማለት አውግዘውታል።የአደሲ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አረጋዊ እንዲሁ “በረቀቀ ሁኔታ የተቀነባበረ ግድያ ነው” ብለውታል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኑ የፖሊስ ሹሙ የአቀናባሪዎቹን ማንነትን ለጊዜው በይፋ አልገለጹም።
የአርቲስት ሀጫሉ ግድያን እና ያስከተለው ቀውስን በተመለከተ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አሚኒስቲ ኢንተርናሽናል በምስራቅ አፍሪካ እና የታላቁ ሀይቆች ም/ል ዳይሬክተር የሆኑት ሳራ ጃክሰን”በሀጫሉ ግድያ ዙሪያ ባለስልጣናት ገለልተኛ፣ፈጣን እና የተሟላ ምርመራ እንዲካሄድ ያድርጉ ዜጎችም መረጃ የማግኘት እድላቸው ይቀጥል ዘንድ የአርቲስቱ አድናቂዎችም ሀዘናቸውን ይገልጹ ዘንድ በአገሪቱ የተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ስራውን በአስቸኳይ ይቀጥል”ሲሉ ጥሪ አቅርቧል።
እንደ ዜና አገልግሎት ሮይተርስ ዘገባ በቀድሞው የፖለቲካ እና የህሊና እስረኛው በአርቲስት ሀጫሉ ላይ የተፈጸመው ግድያ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ዋንኛ የፖለቲካ መደብ የሆነችው ኦሮሚያን ክፉኛ ያወካት ሲሆን በአንድ ወቅት የጠ/ሚ/ር አብይ ደጋፊ የነበረው፣ የቀድሞው የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ ዋና ሀላፊ እና አክቲቪስት የኦሮሞ ፌደራል ኮንግረስን በቅርቡ የተቀናቀነው ጁዋር መሀመድ እና የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባን ለእስራት ዳርጓቸዋል።ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ” ከጁዋር ጠባቂዎች የጦር መሳሪያዎች እና የመገናኛ ራዲዮኖች ተነጥቋል “ብሏል። ጁዋር ቀደም ሲል ይመራው የነበረው የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ዎርክም ቢሮው በፖሊስ በመወረሩ እና ሰራተኞቹ በመታሰራቸው ስርጭቱን ከአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት ለማስተላለፍ ተገዷል ተብሏል።
መቀመጫውን በኒዮርክ ከተማ ያደረገው ለጋዜጠኞች መብት የሚከራከረው ሲፒጄ የኦሮሞ ሚዲያ ኔት ወርክ በጸጥታ ኃይሎች መወረር ፣ጋዜጠኞች መታሰር እና የኢንተርኔት አገልግሎት በኣብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች መቋረጥ ድርጊትን በተመለከት ” የቀድሞ የሳንሱር ስርአትን እንዳይደገም”በማለት በጽኑ አውግዟል።
አዲስ አበባ የተከሰተው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የአዳማ ከተማን ጨምሮ በእንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች በንብረት ላይ ውድመት ያስከተለ ሲሆን በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል ሀረር ከተማ ውስጥ የሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ አባት እና የሀረር ገዢ የነበሩት የራስ መኮንን ወ/ሚካኤል ጉዲሳ የመታሰቢያ ሀውልትን ተቃዋሚዎች ጥቃት እንዳደረሱበት፣በተመሳሳይ ተቃውሞ ጥቃት በታላቋ ብሪታኒያ ሎንዶን ከተማ ውስጥ የሚገኘው እና በቀኃስ ዘመን የተገዛው የኢትዮጵያ ኢንባሲ ለተቃውሞ ወደ ስፍራው የዘለቁ ተቃዋሚዎች በአካባቢው ከነበሩ የጸጥታ ኃይሎች ቁጥር እና ቁጥጥር ውጪ በመሆን የግርማዊነታቸውን ምስል እንደሰባበሩት ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማን በማውረድ በምትኩ ለአጭር ጊዜያት የኦነግ አርማን እንደሰቀሉ እና ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ስድስት የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች በእንግሊዝ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና የተወሰኑ ተቃዋሚዎች ዳግም ወደ ኢንባሲው እንቁላል በመያዝ ለተቃውሞ መምጣታቸውን የአይን እማኞች ለህብር ራዲዮ ተባባሪ ገልጸዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ የሰላሳ አራት አመቱ ፣ባለትዳር እና የሁለት ልጆች አባት የሆነው አርቲስት አጫሉ ሁንዴሳ በታጣቂዎች ህይወቱ መቀጠፍ ያስቆጣቸው በአሜሪካ፣ሚኒስቶ ግዛት የሚኖሩ ሁለት መቶ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ኮሚኒቲ አባላት እና የሀጫሉ አድናቂዎች “ፍትህ ለአጫሉ” በማለት በቅዱስ ጳውሎስ (ሴያንት ፖል) ክፍለ ከተማ ተሰባስበው ተቃውሟቸውን እና ሀዘናቸውን በሰላማዊ መንገድ መግለጻቸውን ሻሃን ጆርናል የተባለው ድህረ ገጽ ዘግቧል።ስልፉን ካስተባበሩት መካከል አንዱ የሆነው ዳሂር ዋቆ”ሀጫሉን ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል፣በደፈናው ለእኔ ትውልድ አዶ(አይከን) እና አባታዊ ታምሳሌት ነው”ብሎታል።
በአጫሉ ግድያ ዙሪያ ከኢትዮጵያኖች ባሻገር ታዋቂ የአሜሪካን ፖለቲከኞችም አስተያየት የሰጡ ሲሆን ትውልደ ሶማሌያዊቷ እና የሚኒሶታ ግዛት የህዝብ እንደራሴ የሆኑት ኢሀን ኦማር “ይህቺ አለም ለህዝቡ የፖለቲካ ግንዛቤ ለማንሳት ለሚሹ ወገኖች፣ቸር አይደለችም፣ የአክቲቪስት እና የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ስራዎች ለኦሮሞዎች እና ለሌሎችም ተስፋ ፈንጥቋል፣በሰላም እረፍ” በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
በሚኒሶታ የቅዱስ ጳውሎስ (ሴያንት ፖል)ከንቲባ የሆኑት ሜልቪን ካርተር በበኩላቸው” በአርቲስት እና አክቲቪስት ሀጫሉ መገደል ምክንያት በሀዘን ውስጥ ለወደቃችሁ የማህበራችን ክፍሎች ሀዘናችሁን መጋራት እንፈልጋላን። “በማለት ሀዘናቸውን እና ድጋፋቸውን ገልጸዋል።