የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ – አዲስ አበባ
ክቡርነትዎ በሰኔ 29፣ 2012 ዓ.ም በእነጃዋርና እስክንድር ጉዳይ ላይ የሰጡትን መግለጫ ስከታትል፤ አግራሞት የጫሩብኝን፣ ያስጉኝን ነገሮች በመመለልቴ፤ መሰረታዊ የህግና የሞራል አምክንዮ ችግሮችን በመታዘቤ፤ የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፌልዎታለሁ።
ጃዋር መሐመድና ግብረ አበሮቹን በተመለከተ
በዚህ የምርመራ መዝገብ ላይ ተጨማሪ አዲስ መረጃዎችን ያላቀረቡ ሲሆን፤ እስካሁን በተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች ሲነገር የነበረውን እንደሚከተለው አቅርበውታል። ከጃዋር መሐመድና በቀለ ገርባ ጋር በአጠቃላይ 36 ተጠርጣሪዎች መታሰራቸውንና ምርመራው መቀጠሉን፤ እስካሁን የተደራጀው የሰውና የሰነድ ማስረጃ የሚያመለክተው፤ የአመጽና ግጭት ጥሪና ዝግጅት ሲደረግ የቆይ መሆኑንና እነዚህም የጥላቻ ንግግሮችን እንደሚያጠቃልሉ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ጃዋርና ግብረ አበሮቹ ከሃጫሉ ሞት ጋር ተያይዞ በቂ የሆን በጦር መሳሪያና በራዲዮ ኮሚኒኬሽን (walkie-talkie) የተደገፈ ዝግጅት አድርገው በመውጣት የሃጫሉን አስክሬን በሃይል በመንጠቅ ወደ አምቦ እንዳይሄድ ከልክለው፤ ወደ ኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት አስክሬኑን ማስገባታቸው፤ ትጥቅ እንዲፈቱ በተደረገው ሂደትም የአንድ ፖሊስ ህይወት ማለፉን፤ በዚህም ሂደት ሚዲያን በተለይም ኦኤምኤንን (OMN) በመጠቀም አስከሬኑ አዲስ አበባ ላይ ነው የሚቀበረው፤ መንግስት አዲስ አበባ ላይ አንዳይቀበር ክልከላ እንዳደረገ ተደርጎ የአምጽ ጥሪዎች መተላለፋቸውን፤ ማስረጃ እንደሰበሰቡ ገልጸዋል።
ከላይ የተገለጹት ነገሮች ከሞላ ጎደል የሚታወቁና የምርመራ ትኩረቱ ህብረተሰቡ የሚጠብቀውንና የህግ የበላይነትን ለማስፈን ከሚደረጉ እርምጃዎችን የሚያቀል ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
በመጀመሪያ ጃዋር የራሱ የጥበቃ ፕሮቶኮል ያለው መሆኑ፤ የሃጫሉ ግድያ የጃዋርን ጥንቃቄ አስፈላጊነት የሚያጎላ መሆኑ ይታወቃል። ከጃዋር የግል ደህንነት ቡድን ላይ የተገኙ የጦርና የመገናኛ መሳሪያዎች (ordinary walkie-talkie equipment)፤ የወንጀል ቅድመ ዝግጅትን የሚያሳዩ አድርጎ መውሰድ፤ ምርምራውን በጀማሪ የአክሽን ፊልም ዳይሬተር የተጻፈ ያስመስለዋል። ክቡርነትዎ፦ እባክዎን የህወሃትን የቀድሞ የፖለቲካ የፍርድ ሂደት ቲያትር አያስታውሱን።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ከክቡርነትዎ ንግግር እጅጉን ያሳሰበኝ የጃዋርና ግብር አበሮቹ የወንጀል ድርጊቶች የሃጫሉን አስከሬን ከማንገላታት ጋር በዋነኝነት የተያያዘ መሆኑ ነው። በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቅጽ 593 ላይ የሙታንን ሰላምና ክብር መንካት በሚለው ርዕስ ስር በንዑስ አንቀጽ (ሀ) የሬሳን አጅብ ሥነ ሥርዓት ያወከ ወይም ያረከሰ፤ ወይም በንዑስ አንቀጽ (መ) ሬሳን … የወሰደ፤ ሰው በቀላል እሥራት ወይም በመቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል። እነ ጃዋር ይህን የወንጀል ድርጊት ስለምፈጸማቸው በቂ መረጃ ስለመኖሩ ብዙ ላያክራክር ይችላል። ሆኖም ግን በዚህ ሁኔታ የነጃዋርን ጥፋት ማየት፤ ህብረተሰቡን ከፍርሃት እንዲወጣ ሲመክሩ ስለራስዎ ፍርሃትም ጭምር እያወሩ ነበር ወይ ያሰኛል።
የጃዋርና ግብር አበሮቹ ዋና ጥፋት የሃጫሉ አስከሬን አሸኛኝትን ማወክ ሳይሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ ጃዋር በኦፊሳላዊ (de jure) ወይም በተግባር (de facto) በሚመራው ቄሮ በሚባል ቡድን የተፋጸመው ግድያና የሽብር ተግባር፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ በኦኤምኤን ሚዲያ ላይ የተላለፈው የዘር ማጥፋት ጥሪ የሚመለከቱ የወንጀል ህግ ድንጋጌዎችን የሚጥሱ ተግባራት ናቸው። ለነዚህም ጥፋቶች የቄሮና የኦኤምኤን ሚዲያ አመራር ተጠያቂነትን መመርምርና፤ ተገቢውን ክስ ማቅረብን ይመለከታል።
ክቡርነትዎ፤ ሌላው በመንግስትዎ አካሄድ ላይ ጥርጣሬ የሚያስነሳው እርምጃ፤ በቄሮ አመራሮችና በኦኤምኤን ጋሻ ጃግሬነት የተካሄደውን ጥፋት፤ የጸጥታ ሀይሎች ሊያስቆሙት ባለመቻላችው ወይም ባለመፈለጋቸው፤ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት (self-defence) በመጠኑም ቢሆን የተፍጨረጨረውን የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ ኢትዮጵያዊ፤ በሕገ መንግስትና በሕገ መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀል (አንቀጽ 238) ማነሳሳት፣ የአባሪነት ሙከራ ማደርግ (አንቀጽ 255)፣ መገፋፋትና መሰናዳት ((አንቀጽ 257) የሚል የክስ ውርጅብኝ፤ በእነ እስክንድርንና ግብረ አበሮቹ ላይ ማውረድ ነው። የእነእስክንድር መታሰር ለራሱም ደህንነት ወይም ለማሟያና ሚዛናዊ ለመምሰል ይሆናል ብለን መላምት ስንሰጥ፤ ክቡርነትዎ እስክንድርና የባለደራስ አባለት፤ ዋነኛ የጥላቻ አጋፋሪዎች ናቸው ሲሉ በሃፍረት ተኮማትሬያለሁ፡፡ የዚህ ፍርደ ገምድልነት ጦስም አጅጉን አሳስቦኛል።
የእነ እስክንድር ጉዳይ ላይ ከመቀጠሌ በፊት፤ ሶስት ከንግግርዎ ያልነበሩ አንኳር ነጥቦችን ልጥቀስ፤
- በሃጫሉም ግድያ ይሁን በሰኔው የይለይለታል ድግስ የውጪ ሀይሎች ሚናን በተመለከተ ዝምታን የመረጡት ጉዳዩ ሙሉ በሙሉ የሀገር ውስጥ ጉዳይ መሆኑን ስለደረሱበት ነው? ከሆነ እሰይ የውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ትብታቡ ስለሚያንስ መፍትሄው አያስቸግረንም ማለት ነው። ታዲይ ምነው ይህን የምስራች ለመንገር ንፉግ ሆኑ?
- የእነጃዋር ወደስቴዲየም/የኦሮሚያ ባህል ማእከል የተደረገ ጉዞ፤ በኦሮሚያ ባለስልጣናት ላይ፤ አምና አማራ ክልል እንደተፈጸመው አይነት የወንድምማማቾች እልቂት ለመፈጸም ነው ተብለን ነበር። በዚህ ጉዳይ ዝም ያሉት እንጃዋር እንደዚህ ዓይነት ጀብደኝነት ስለማይነካካቸው ነው ወይስ የመንግስትዎ የተለመደው የጅብ ችኩልነት ቀንድ አስነክሶት ነው? ክቡርነትዎ ፦ እባክዎ በምርምራ ላይ ባለ መዝገብ የፖለቲካ ትንተና ወይም ምዘና መስጠቱን ያቁሙ፤ አለዚያ ያወገዛችሁትን የሎሌነት ጊዜ አመለካከትን፤ በጌትነትና የ“ነጻነት” ጊዜ መድገም ይሆንብዎታል፡፡
- በመጀመሪያ መግለጫዎ ላይ የጠቀሱትን፤ የእነ ጃዋር በጥቅምቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል ምርመራ ስለመከፈቱ፤ እና የኦኤምኤን የወንጀል ኃላፊነትም፤ በሁለተኛው መግለጫዎ ላይ ያሳዩት ዝምታ አሳስቦኛውል።
እስክንድር ነጋና ግብረ አበሮቹን በተመለከተ
ክቡርነትዎ፦ እስክንድር ነጋ (ከባላደራ ወይም ባልደራስ) ከ5 ግብረ አበሮቹ ጋር መታሰሩን ገለጸው፤ ስለነእስክንድር የሚከተለውን ተናግረዋል፤
በእነኚህ ስድስት ሰዎች ላይም እና በእነሱ ምክንያት ወደ አመጽ የወጡትን ወጣቾች በተመለከተ በአጠቃላይ ምርመራው እየሄደ ነው ያለው፤ ወጣቶቹ ከዚህ በፊት በተሰጠው መረጃ መሰረት ከ900 በላይ የሚሆኑ ናቸው። በእነ እስክንድር ነጋና ከእነሱ ጋር ተያይዞ ግን ስድስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው፤ ከዚህ በፊት ሲያደርጉ የነበሩት የአመጽ ጥሪ፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ ብሔር ተኮር የጥላቻ ንግግሮችን፣ መግለጫዎችን፣ ትንተናዎችን፣ ጽሁፎችን፣ መልዕክቶችን ከዚሁ አመጽ ስራ ጋራ ተያይዞ፤ በዕለቱ የሃጫሉን ሞት እና ለሃዘን የወጣውን ህዝብ፤ ለዓመጽ እንደመጣ፤ ቄሮ ሊያጠቃህ ነው፤ ወደ አዲስ አበባ ገብቷል፤ ራስህን ተከላከል በሚል ለወጣቾች ተልዕኮ መሰጠቱን፣ ገንዘብ መሰጠቱን፤ ገንዘብ በመስጠት ሂደትም ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎችም ጭምር በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራቸው እየተደረገ ነው ያለው ማለት ነው።
ይሄ ንግግር አመጽ ያካሄደው እስክንድርና በሱ የተደራጁ የአዲስ አበባ ወጣቶች መሆናቸውን፤ እነዚህ ጸረ ሰላም ሃይሎች በሰላም ወዳዱ፤ ነፍጠኛ ተኮር ስድቦችንና መፈክሮችን እያሰማ፤ በኦኤምኤን ቻናል ላይ ሃጫሉን አዲስ አበባ በመቅበር፤ ከቀብር መልስ የጨካኙ ምኒልክ ሃውልትን በማፍረስ፤ አዲስ አበባን በሰላማዊ መንገድ የደም አውድማ ለማድረግ የሚፎክር፤ በመንገድ ላይ ያገኝውን በአሮሞ መሬት ላይ በብዝበዛ የተፈራ የነፍጠኞች ንብረት ሰላማዊ በሆኑ አለቶችና በትሮች እየበረቃቀሰ/እየሰባበረ ሃዘኑን ሲገልጽ የነበረውን ቄሮ፤ በማሸበር ከባድ ወንጀል ማስረጃ እንደተገኝባቸው ገልጸውልናል። እንደዚህ ያለ ነጭ ውሸት ተገቢ አይደለም ወይም ቀልድ ነው። ቀልዱ ይቅርና፤ የህግ ማስከበር፣ የሚሊዮን ሰላማዊ ዜጎች ህይወት ማዳን፤ አገር ማዳን ቅድሚያ ይሰጠው።
ክቡርነትዎ፦ በዚህ ረገደ የተናገሩት ቀልድ ማባሪያ ያለው አይመስልም። እነ እስክንድር “አዲስ አበባ ላይ ቄሮ ሊፈጅህ ነው በሚል ብሄር ተኮር ጥላቻዎችንና የተለያዩ መልዕክቶችን በመስጠት ይሄ የአምጽ እንቅስቃሴው እንዳይቋረጥና ቀጣይ እንዲሆን የሃገርን ደህንነት” አደጋ ላይ የሚጥል ስራ ሲሰሩ እንደነበር መረጃ እንዳለዎት፤ እንደውም የነእስክንድር ስራ ከነጃዋርና ሌሎች በ3ቱ ሰኔዎች ችግር ሊፈጥሩ ካሰቡ ሀይሎች ስራዎች ጋር ትስስር እንዳለው በገደምዳሜ ጠቁመውናል፡፡ ይሄ የአብዬን ለእምዬ መስጠት መንግስተዎ ቀድም ብሎ የእነጃዋር ቡድን የሰኔ ላይ ይለያል ድግስ አዘጋጅቶ እነደነበር ከነገረን ታሪክ ጋር ይጋጫል። አሁን ደግሞ የዚህ ድግስ ባለቤት ባልደራስም ነበር ሲሉን፤ የሞራልም የአምክንዮም ችግርን ያሳብቃል። በሚቀጥለው መግለጫዎ በሰኔ ይለያል ድግስ ባለቤት ጃዎር ወይስ እስክንድር የሚለውን በግልጽና ሃቅ እንዲነግሩን እማጸናለሁ።
ሃዘንተኛ ቄሮን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያጠቃ ጀሌ ወንጀለኝነትን በተመለከተ
ክቡርነትዎ፦ የሚከተለው ንግግርዎ ምን ያህል ከእውነታ መራቅዎንና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በብሄራቸው ብቻ ህይወታቸውን፣ አካላቸውንና ጥሪታችውን ላጡ አማሮች፣ ለዘብተኛ ኦሮሞዎች እና ጉራጌዎች ያለዎትን ንቀት ያሳብቃል።፡
አምስተኛው በሃጫሉ ሞት ምክንያት ተደናግጦ ሃዘኑን ሊገልጽ በወጣው ሰው ላይ፤ በዚህ ህዝብ ላይ በተለየ ሁኔታ ተደራጅተው፣ ጥቃት ለማድረስ፣ ግጭት ለማስነሳት ተዘጋጅተው፣ ተደራጅተው የነበሩ ሰዎች፣ በንጹሃን ላይ ያደሱት ጥቃት፣ ህልፈት ህይወት በተወሰኑ ከተሞች ላይ ታይቷል፤ እንደሌላው ጊዜ ሳይሆን ምንም ማምለጥ አልቻሉም በሚባልበት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።
እንደው በየትኛው አመክንዮና የዓለም ታሪክ ነው በቁጥር አናሳ የሆን ብሄር ከእሱ እጅጉን በሚበልጠውን ቡድን ጋር ግጭት ለማስነሳት የሚዘጋጀውና የሚያጠቃው? በተወሰኑ የተባሉት ከተሞችን ስም ምስጢራው ማድረግዎ አግባብ አይደለም። ይህም የተጀመረው ምርመራ ሙያዊ በሆነ መልኩ ሳይሆን ለጊዜያዊ ፖለቲካ ፍጆታ የሚሰራ ያስመስለዋል።፡
ክቡርነትዎ፦ በአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በሰኔ 30 ስርጭት፤ አቶ ደረጀ የተባሉ የደራ ከተማ ነዋሪ በሰኔ 23 ቀን፤ ሊጠይቃቸው የመጣውን ልጃቸው ማሰረሻን በአሰቃቂ ሁኒታ፤ በጽንፋኛ የኦሮሞ ብሄረተኞች አማራ በመሆናቸው ብቻ አንደተገደለባችው የተናገሩትን፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሸማግሌ እንባ ያቀረቡትን የፍረዱኝ ምልጃ ላይ መሳለቅ ይቅር። በአሳሳ ከተማ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት አማራው አዛውንት፤ የአገር አባት አቶ ተፈሪ አጥናፉ ሃዘኑን በድንጋጤ የሚገልጸው ቄሮን ተደራጅትው ግጭት በመተንኮሳቸው ነው የተገደሉት የሚሉት በምን ዓይነት ሞራል ነው? የሻሽመኔ ቄሮ ያንን ሁሉ የከተማውን የአማራ ንብረት የዘረፈው እና ያቃጠለው ሃዘኑን በድንጋጤ ሲገልጽ ነው ሲሉን፤ እረ በእግዜር!!
ህዝቡ ከፍርሃት መውጣት ያለበት ስለመሆኑ
ክቡርነትዎ፦ ሕዝቡ ለጸጥታ አካላት የሚሰጥውን ጥቆማዎች በማመስገን ህዝቡ ከፍርሃት ውስጥ መውጣት አለበት ብለው መክረውናል። በጄ፤ ንግግርዎን እነጃዋርንና ግብረ አበሮቹን በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 269 የተደነገገውን የዘርን ማጥፋት ወንጀል ምርመራ በመከፈት፤ ገለልተኛና ታዓማኒ በሆን መልኩ ምርምራውን በማካሄድ ወይም እንዲካሄድ በመፍቀድ፤ በተግባር ድፍረትዎን ያስመስክሩ። በዝዋይ(ባቱ) በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት የአንድ ቤተሰብ አባላት (ወ/ሮ ጸሃይ መንግስቱ ቀጸላ፣ አቶ ገለታው አውላቸው፣ ወጣት ነጻነት ገለታው አውላቸው፣ ወጣት ሳሙኤል ገለታው አውላቸውና ወጣት ዋስይሁን አግዜ) ዘመዶችን ከጋዜጠኞች ጋር እንኳን እንዳያወሩ ማስፈራሪያ የሚሰጥ ቡድን በኦሮሚያ በሚያንዣብበት ሁኔታ፤ ህዝቡን ደፋር ሁኑ ማለት ብቻ ድፍረት አያመጣም፤ መተማምኛ አይሰጥም።
የህዝብ ፍርሃት የመንግስት ጸጥታንና የህግ የበላይነት ማስከበር አለመቻል ማሳያ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። የተወሰኑ የመንግስት ባልስለጣናት የብሄር ተኮር ጥቃቱ ተባባሪ ናቸው ብሎ የሚያምን ህብረተሰብን፤ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች አድሎአዊ ወገንተኝነት በሚያሳዩበት ሁኔታ፤ መንግስት ተመሳሳይ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን የፈጸሙ ሰዎችን ታማኝ በሆነ ሕግን በተከተለ የፍርድ ሥርዓት ተጠያቂ የማድረግ ፍላጎትም ልምድም የሌለው መንግስት ህዝብን ፊሪ አትሁን ብሎ መምክር የራሱን ፈሪነትና ልፍስፍስነት ከማሳየት ያለፈ ፋይዳ የለውም።፡
የሃጫሉ ግድያ በገለልተኛ አጣሪ እንዲታይ መጠየቅ ወንጀል ስለመሆኑ
ክቡርነትዎ፦ የሃጫሉ ግድያ ጉዳይና ከዛ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በገለልተኛና ተዓማኝነት ባለው ሁኔታ ይከናወን ብሎ መጠየቅ “ሕገ ወጥ” ጥሪ በመሆኑ ያስጠይቃል በማለት አጥብቀው አሳስበዋል። አንድ ነገር ህገ ወጥ ነው ሲባል ያንን ድርጊት መፈጸም በሕግ ክልክል መሆኑን ያመለክታል። ይህ አካሄድ ማንኛውንም የፖለቲካ ጥያቄ ህገ ወጥ ወይም ክልክል የሚያደርግ ነው። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ተራ የመንደር ጎረምሳ ማስፈራሪያ ከመስጠት የመድብለ ፖርቲ ሥርዓቱን አፍርሶ እንደ ደርግ የአንድ ፖርቲ አምባገነነትን ማወጅ ሳይሻል አይቀርም። ወይንም ይሄ ንግግርዎ አሁንስ መንግስቱን መስለከኝ ያሉትን፤ የቀዶሞው ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ (አፈሩ ይቅለላቸው) ያስታውሰኛል።
ክቡርነትዎ፦ በሌሎች የዳበረ የህግ ሥርዓት ባላቸው አገሮች እንኳን ትልልቅ የፖለቲካ ግድያን የሚያጣራ ገለተኛ አካል እንዲቋቋም መጠየቅ እንኳንስ ወንጀል ሊሆን የተለመድ የፖለቲካ መተማመኛ እርምጃ ነው። ለምሳሌ፦ በአሜሪካ የፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬንዲን ግድያ ለማጣራት የዋረን ኮሚሽን የሚባል አካል በመንግስት ተቋቁሞ የ888 ገጽ ሪፖርት በማቅረብ ግድያው በግለሰብ ደረጃ ብቻ የታቀደ መሆኑን በማመልከት ሥራውን አጠናቋል:: ብዙ ተመሳሳይ ምሳሌዎችን መስጠት ይቻላል፡፡ በአገራችንም፤ የጋምቤላው የ95 ጭፍጨፋ እንኳን የሚያጣራ ኮሚሽን (ፍትህ ሚኒስተር ስራዬ ነው እንኳን ብሎ በወቅቱ ጥያቄ ያልቀረበበት) ተቋቁሞ ነበር፡፡
ክቡርነትዎ ካልለገሙ እንደሚረዱት፦ ይህ ጥያቄ የመነጨው፤ በፍትህ ስርአቱ ላይ እምነት ከማጣት ነው፡፡ የፍትህ ሥርዓቱን ተዓማኒነት ግምት ውስጥ በማስገባት የሃጫሉ ግድያን በገለልተኛ አካል ይጣራ ማለት ህዝቡን የማደናገርና ግራ የማጋባት ስራ ነው ብለዋል። ይህ የተለመደው የኢሕአዴግ የግራ ዘመም የእኔ አውቅልሃለሁ አመለካከት ወደ ብልጽግና ፓርቲ መተላለፉን ያሳያል።እንደሚታወቀው ርስዎ ራስዎ፤ የጠቅላይ ዐ/ህግ የብልፅግና ፖለቲካ ፓርቲ አባል እና ስራ አስፈፃሚ ነዎት፡፡ (ከዚህ ቀደም ብርሃኑ ፀጋዬ የኦዴፓውን እንደነበረው ሁሉ)። ይህም በተደጋጋሚ የመንግስትና የፓርቲ መደበላለቅ ላይ ከሚነሳው ትችት ባለፈ፣ የዚህ ተቋም ገለልተኛነትና ከፖለቲካ ጣልቃ ገብት የፀዳ መሆን አለመቻሉ ላይ ትልቅ ማሳያ ነው። በተለይ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ክሶች ላይ። ስለዚህ በእንዲህ ዓይነቱ ዓውድ የገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ይመስረት የሚለው ግፊት እጅጉን የሚደገፍ እንጂ ሊወቀስ አይገባውም። ይህንን እንደ ህገወጥ ማየት በራሱ ለህግ እና ህጋዊ አሰራር ጨለምተኛ የሆነ አተያይ የሚያመላክት ነው። በተለይም ይህ የዐብይ አስተዳደር ከባለፈው ጨቋኝ ስርዓት ውርስ አድርጎ የቀጠለው ክፉ ተግባር ነው።
ከላይ የቀረበው የገለልተኛ ጥያቄ ላይ እንደመፍትሄ አማራጭ የገለልተኛ መርማሪ ኮሚሽን መቋቋም ከፍ ያለ የፖለቲካና የህግ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነና በተለይም የወንጀል ክስ ምርመራና ክስ ማቅረብ ስራ የጠቅላይ ዐህግ ቢሮ ከመነሻውም ከፖለቲካ ተፅዕኖ እንዲላቀቅ ለዘመናት ሲጠየቅ የነበረው የወንጀል ፍትህ አስተዳዳር (criminal justice administration) አንዱ አካል መሆኑ፣ ጉዳዩ ከተራ የወንጀል ክስ ባለፈ የተቀናጀ እና በመንግስት የሃላፊበት ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ሰዎች ተሳትፎ እንደሌላቸው ተጣርቶ መተማመኛ ሊገኝ የሚችልበት ብቸኛ መንገድ በመሆኑ ነው።
ክቡርነትዎ፦ ይቺ ቀላል ነገር ሳትሆን ህዝብን በማደናገር የፍትህ ሥርዓቱን ተዓማኒነትን የሚጎዳው የሚከተሉት የመንግስትዎ ከባድ ህጸጾች ናቸው፤
- ጠ/ሚንስትራችን አስረን አንመረምርም፤ ምርምረን እናስራለን ብለው ቃል ከገቡልን በኃላ አስሮ መመርመርንና ፍሬ የሌለውን ምርምራ በተመለከት ተከታታይ ጋዜጣዊ መግለጫ መለማመዳችን፤
- አንገርፍም ብለው ጠ/ምንስትራችን ቃል በገቡ ማግስት፤ ወያኔ ያልገረፈውን እስክንድርን ወጉን ማቅመስ፤
- ጃዋርና በቀለ ገርባን እስካሁን ድረስ በጠበቃ እንዲጎበኙ አለመፍቀድ፤
- ይልቃል ጌትነት አስሮ የታሰረበትን ቦታ እንኳን ለቤተሰቡ አለመናገር፤ እና የመሳሰሉት።
ማጠቃለያ
ክቡርነትዎ፦ የአዳማ ከንቲባ ሆነው ያሳዩት የአመራር ብቃትና ያስመዛግቡትን አዎንታዊ ውጤት በፍትሕ ዘርፉም ለመድገም በታሪክ የተሰጠዎትን ኋላፊነት ከላይ የተጠቀሱትንና የሌሎች የህግ ሊቃውንትን ምክር በመስማት፤ ህገ መንግስቱን በማክበርና ለህግ የበላይነት ቀናኢ በመሆን አሻራዎን ያሳርፉ። የታሪክ ህዳግ ከመሆን ይድኑ ዘንድ የፍትሕ ከበሮ ትጮሃለች።
ከሰላምታ ጋር፤
ረቂቅ ይሁን
ሐምሌ 3፣ 2012