ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣውን የዘረኝነት ፕሮፐጋንዳን በሚያራምዱ ሚዲያዎች ላይ መንግሥት ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።
“በየሚዲያው በሚረጨው መርዝ ዜጎች ህይወታቸው የሚቀጠፍበትና ኢትዮጵያ የምትፈርስበት እድል ሊፈቀድ አይደገባም” በማለት በጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ሴክተሪያት በኩል አቋሙን የገለጸው የጠቅላይ ማኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት፤ “የሚኖሩበትን ሕዝብና አገር እያጫረሱ፣ እንዲፈርስ እየጣሩ የሚዲያ ተቋም ነን ሊሉ አይችሉም፤ ጋዜጠኛ ነን ሊሉም አይችሉምና መንግሥት በዚህ መሰል ግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል” ሲል አስታውቋል።
ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግንድያ በኋላ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ መንግሥት በመላው አገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ለበርካታ ቀናት ተዘግቶ የቆየበትን ምክንያት አስመልክቶ የመንግሥትን አቋም የገለጹት የፕሬስ ሴክተሪያት ቢሮ ሓላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን፤ ኢንተርኔት የተዘጋው ለጸጥታ ሲባል መሆኑን ጠቁመው የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ሲረጋገጥ ሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚጀመር ተናግረዋል።
“አሁንም ቢሆን ፌስቡክ የሚባለውን ያዝ አድርጉልን። በብሔርና በሃይማኖት ላይ የክተት ጥሪ እየተጠራ ነው፣ የሚሉ አስተያየቶች ከሕዝብ እየተሰጠን ነው” ያሉት ሓላፊው በሕዝቡ ዘንድ ከኢንተርኔት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስጋት በመኖሩ በዚህ ወቅት ኢንተርኔት መልቀቁ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ጠቁመዋል።
አቶ ንጉሡ ጥላሁን ይህን ይበሉ እንጂ ከትናንት ከሰዐት በኋላ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ በከፊል የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍት ተደርጓል። የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ በተለያዩ ሥፍራዎች ላይ የዋይፋይ ኢንተርኔት አገልግሎት ክፍት ቢደረግም በርካቶች የሚጠቀሙት የሞባይል ዳታ የኢንተርኔት አገልግሎት ግን እስካሁን ድረስ እንደተዘጋ መሆኑን ማረጋገጥ ችለናል።