ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከሳምንት በፊት ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ቁጥር 5 ሺኅ እንደሚደርስ ተነገረ።
በአሁኑ ጊዜ የአገሪቱ የጸጥታ ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን ያሳወቀው መንግሥት፤ ከድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ተከስቶ በነበረው ሁከት በሰው እና በንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር 5 ሺህ ገደማ የደረሰ ቢሆንም በቀጣይም ተጠርጣሪዎችን የመያዙ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ብሏል።
“የጸጥታ መዋቅሩ የማያዳግም እርምጃ እየወሰደ ነው” ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት አሁንም በጸጥታ አካሉ እየተፈለጉ ያሉ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሶ፤ ተከስቶ በነበረው ሁከት በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ከፌደራል እና ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተወጣጣ አካል አለመረጋጋቱ አጋጥሞባቸው ወደነበሩት ስፍራዎች ተጉዞ ሥራ መጀመሩንም አስታውቋል።