ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ሰላም ከራቃት ዓመታት ባስቆጠረችው የመን የሚገኙ በዐሥር ሺኅዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ በችግር ላይ መሆናቸው ተነገረ።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ባወጣው መግለጫ መሠረት ከእነዚህ በየመን ከሚገኙ ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።
ዓለም ዐቀፉ የስደተኞች ድርጅት ቢያንስ 14 ሺኅ 500 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች መሰረታዊ የጤና እና የንፁህ ውሃ አገልግሎት በማያገኙበት ሁኔታ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ በከፋ ችግር ላይ እንዲወድቁ ተዳርገዋል ብሏል።
የመን በወረርሽኙ ሳቢያ ድንበሮቿን በመዝጋቷ ስደተኞቹ ያለ ፈቃዳቸው ወደ አደን ፣ ማሪብ፣ ላህጅ እና ሳዓዳ እንዲሄዱ መገደዳቸውን እና በእነዚህ ቦታዎችም ስደተኞቹ በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ከወጣው መግለጫ መረዳት ተችሏል።
በዚህን መሰሉ አስከፊ መከራ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ቫይረሱ እንዳለባቸው በማሰብ ፤ መገለልና እና ጥቃት እንደ ደረሰባቸው ዓለም ዐቀፉ ድርጅት አስታውቋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በየመን የሚገኙ ስደተኞች የቃል እና አካላዊ ጥቃቶች እየደረሰባቸው፣ የእስር ጊዜያቸው እየጨመረ፣ የእንቅስቃሴ ገደብ ከመጣል ባሻገር፤ እንዲሁም ያለፈቃዳቸው መሰረተ ልማት በሌለባቸው አካባቢዎች እንዲሄዱ መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ባለፈው ዓመት ከአፍሪካ ቀንድ አገራት፤ አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ የሆኑ 138 ሺኅ ስደተኞች ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት በማለም የመን መግባታቸው መዘገቡ አይዘነጋም።