ቅሬታ የቀረበባቸው ተቋማት ደብዳቤ አንቀበልም ማለታቸውን ዕንባ ጠባቂ  ተቋም አስታወቀ

ቅሬታ የቀረበባቸው ተቋማት ደብዳቤ አንቀበልም ማለታቸውን ዕንባ ጠባቂ  ተቋም አስታወቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተለያዩ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ኮሮና ቫይረስን እንደ ምክንያት በመጠቀም ሥራዬን እያስተጓጎሉብኝ ነው ሲል ከሰሰ።

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተወሰነ የሰው ኃይል አገልግሎት እንዲሰጡ የተወሰነ ቢሆንም ብዙዎቹ ይህንን እያከበሩ አይደለም ያሉት የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ቀኜ፤ ተቋማቸው ከዜጎች የቀረቡለትን ቅሬታዎች መነሻ በማድረግ ሰነድ ለመፈተሽ እና ምርመራ ለማካሄድ በሞከረበት አጋጣሚ፣ በኮሮና ምክንያት ሠራተኞች ቢሮ አልገቡም የሚል ምላሽ እየተሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ምክንያት በሥራዬ ላይ እንቅፋት ሆኗል ያለው ዕንባ ጠባቂው  ተቋም፤ በርከት ያሉ መሥሪያ ቤቶች በቀረበባቸው ቅሬታ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ የሚጻፍላቸውን ደብዳቤ በ”ኤሌክትሮኒክስ መላ” ወይም ኢሜይል ካልሆነ በስተቀር አንቀበልም እያሉ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውንም አስታውቋል።
እንዲህ ዓይነቱ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ዳተኝነት ተቋሙ የዜጎችን ቅሬታ ቶሎ ቶሎ አጣርቶ መፍትኄ እንዳይሰጥ አድርጓል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በኢሜይል ካልሆነ ደብዳቤ አንቀበልም ከሚሉ ተቋማት የተወሰኑት ከተቋሙ የሚደርሳቸው ማስጠንቀቂያን ተከትሎ ሀሳባቸውን እየቀየሩ መሆኑን ጠቁመው፣ እስከ መጨረሻው በአካል የሚሰጥ ደብዳቤን አንቀበልም የሚሉ መሥሪያ ቤቶችን ጉዳይ ደግሞ ተቋሙ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሪፖርት ያደርጋል ብለዋል።
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ከቀበሌ እስከ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ባሉ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ላይ በተገልጋዮች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን መነሻ በማድረግ ማጣራት አካሂዶ የመፍትኄ ሀሳብ የሚያቀርብ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።

LEAVE A REPLY