የህዳሴው ግድብ ዉሃ ሙሌት ተጀምሯል የተባለው ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን ዶ/ር ስለሺ በቀለ...

የህዳሴው ግድብ ዉሃ ሙሌት ተጀምሯል የተባለው ዘገባ የተሳሳተ መሆኑን ዶ/ር ስለሺ በቀለ ገለጹ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና–  የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሌት መጀመሩን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ማስታወቁን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ቢዘግቡትም የተቋሙ ዋና  ሥራ አስፈጻሚ ግን የውሃ ሙሌቱ በይፋ አልተጀመረም ብለዋል።

ሚኒስትሩን ዶ/ር ስለሺ በቀለን ዋቢ አድርገው የአገር ውስጥ ሚዲያዎች እንደዘገቡት የውሃ ሙሌቱ የግድቡን ተፈጥሯዊ የግንባታ ሂደት በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸው የነበረ ቢሆንም ኢንጂነሩ ግን ይህን ዘገባ ዛሬ ለቢቢሲ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ አስተባብለዋል።
ግድቡ ሙሌት መጀመሩን አስመልክቶ  የወጣው ዘገባ የተሳሳተ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ “ዘገባው በስህተት የወጣ ነው፤ የራስ ትርጉም ተጨምሮበታል። ግድቡ ግንባታው አሁን የደረሰበት ደርሷል፤ ግድቡ ውሃ ይይዛል እንጂ በይፋ የተጀመረ ነገር የለም” ሲሉ ተናግረዋል።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በተመሳሳይ መልኩ ለአሶሺየትድ ፕሬስ፤ “እነዚህ የሳተላይት ምስሎች የሚያሳዩት ከፍተኛ ዝናብ መኖሩንና ከግድቡ ከሚወጣው ይልቅ ግድቡ ውስጥ የሚገባው መጨመሩን ነው ” ማለታቸው ተሰምቷል።
 ባለፈው ዓመት ውሃው ያልፍ የነበረው በ520 ከፍታ ላይ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት 560 ከፍታ ላይ መድረሱን ያስረዱት ሚኒስትሩ፤ ከ560 ከፍታ በታች ያለው ውሃ ግድቡ ውስጥ የሚቀር እንደሆነና ሙሌቱም ከግንባታው ሂደት ጋር የማይነጣጠል ነው ሲሉ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች መዘገባቸውን አስታውሰዋል።
 ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ይህ ስምምነት ሳይደረስ የውሃ ሙሌቱ ይጀመራል ወይ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፤  “አሁን የምሰጠው ነገር የለም፤ ጊዜው ሲደርስ ይታያል። በሦስቱ አገራት መካከል ሲካሄድ የነበረው ድርድር በቀጣይነት ስለሚካሄድ በዚህ ወቅት እንዲህ ነው ብሎ መደምደም ይከብዳል” ብለዋል።

LEAVE A REPLY