ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከሁለት ሳምንት በፊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የአቶ ጃዋር መሐመድን ጉዳይን ዛሬ የተመለከተው ፍርድ ቤት ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ ፈቀደ።
አወዛጋቢው ፖለቲከኛ ጃዋር መሀመድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ፖሊስ የጀመረውን ምርመራ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ቀናት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
በአንጻሩ የጃዋር ጠበቃ ደንበኛቸው በዋስ ከእሰር ቤት ውጪ ሆኖ ጉዳዩን መከታተል እንዲችል እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀው የነበረ ቢሆንም፤ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ያቀረበውን የተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ጥያቄ በመቀበል የዋስትናውን ጉዳይ ውድቅ አድርጎታል።
በችሎቱ የተከሳሽ ጠበቆች ደንበኛቸው ምግብ ከቤተሰቡ የሚቀርብለት ቢሆንም፣ ግንኙነታቸው በርቀት ስለሆነ ባለበት ከርቀት አይቶ የመለየት ችግር አኳያ ቤተሰቦቹን በቅርበት እንዲያገኝ እንዳልተፈቀደለት ለችሎቱ አስረድተዋል።
ጉዳዮን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጠው ፖሊስ ታሳሪዎችና ጠያቂዎች መካከል መቀራረብ እንዳይኖር የተደረገው፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቆጣጠር በወጣው ደንብ መሰረት መሆኑን ገልጿል።
አቶ ጃዋር የታሰረበት ክፍል በቂ ብርሃን የሌለው መሆኑን፣ መጸዳጃ ቤት የመጠቀም ችግርም መኖሩን ያነሱት የተከሳሽ ጠበቆች፤ በተጨማሪም ደንበኛቸው ጥፋተኝነታቸው ገና ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ምስላቸው እየቀረበ ዘገባዎች እየቀረቡ ስለሆነ ፍርድ ቤቱም ይህንን ድርጊት እንዲያስቆምላቸው ጠይቀዋል።
አቤቱታውን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ለእስረኞች መጸዳጃ ቤትንና በማረፊያ ክፍሎች ውስጥ ያለውን ብርሃን በተመለከተ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በመገናኛ ብዙሃን ላይ ስለቀረበው አቤቱታ ግን ጠበቆች ቅሬታ አለብን ያሏቸውን ተቋማት በቀጣይ ቀጠሮ በስም ለይተው እንዲያቀርቡ አዝዟል።
በመጨረሻም ፖሊስ ለምርመራ የጠየቀውን የ14 ቀናት ጊዜ ፈቅዶ ጉዳዩን ለመመልከት ሐምሌ 23/2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ሥራውን አጠናቋል።