ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በምታስገነባው የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት የተነሳ ግብፅ ወደ ጦርነት የምትገባበት ዕድል እንደማይኖር ባለሙያዎች እየተናገሩ ናቸው።
የግድቡ ውሃ መጨመርንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በውሃ ፖለቲካ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በላቸው፤ ግድቡ ውሃ መያዙን ማረጋገጣችንን ተከትሎ ከግብጽ በኩል የተለየ ምላሽ መጠበቅ እንችላለን? ወይ በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ምንም የተለየ ምላሽ እንደማይኖር ሌላ ጊዜም እንደሚሉት ማስፈራራት የተለመደው ተግባራቸው ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ አስረድተዋል።
” በአረብ አገራት በኩል ጫና ሊያሳድሩብን ይሞክሩ ይሆናል። ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ግጭቶችን በማባባስ ወደዚያ ውጥረት ሊያስገቡን ይሞክሩ ይሆናል” ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አገር ውስጥ ያሉትን አንዳንድ የተቃዋሚ ድርጅቶችንም አሁን ያለውን ሁናቴ ተጠቅመው እርስ በእርሳችን ማተራመስ ይፈልጉ ይሆናል እንጂ፤ ከዚያ በተረፈ በቀጥታ ጥቃት የሚባል ነገር እርሱ በተግባር ሊታይ የማይቻል ሲሉ ገልጸዋል።
“አሁን የሚያጣላው ነገር ግድብ ውሃ መሙላቱ አይደለም። ከተሞላ በኋላ የሚለቀቀው ውሃ ነው ትልቁ ችግር። እነርሱ የሚፈልጉት ከተሞላ በኋላ የሚለቀቀው ውሃ መጠኑን አሁኑኑ እንወቀው ነው። እኛ ደግሞ ይህንን ግድብ ብቻ አይደለም የምንሠራው ከግድቡ በላይ ሌሎች ወደ ፊት ለምንሠራቸው ፕሮጀክቶች ውሃ ሲያስፈልገን መጠቀም አለብን ስለምንል አሁኑኑ ይህን ያህል ውሃ እንለቅላችኋለን ብለን ቃል መግባት የለብንም ነው። ለነገሩ እርሱ የኛ የሱዳንና የግብጽ ጉዳይም አይደለም። የ11 የተፋሰስ አገራት ጉዳይ ስለሆነ ብቻችንም የሚለቀቀው ውሃ ላይም መስማማት አይገባንም።” በማለት ባለሙያው እውነታውን አስቀምጠዋል።