ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ፓርቲ ሊቀ መንበር እስክንድር ነጋ፣ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባና ስንታየሁ ቸኮል ለሁለት ሳምንታት ከነበሩበት የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን እስር ቤት ወደ ሌላ ሥፍራ መዘዋወራቸው ተሰማ።
የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በአዲስ አበባና በተለያዮ የኦሮሚያ ከተሞች ኹከት ፈጥራችኋል፣ ወጣቶችን አደራጅታችኋል (የክሳቸው መጠን ልዮነት ቢኖረውም) በሚል የተጠረጠሩት እነዚህ ግለሰቦችና ግብረ አበር ናችሁ የተባሉ ሰዎች ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የ14 ቀን ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ይታወቃል።
እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ በሚገኙ ጠባብና ጨለማ ክፍሎች ውስጥ ታስረው የነበሩት እስክንድር ነጋ ፣ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባና ስንታየሁ ቸኮል ረፋዱ ላይ ሜክሲኮ አካባቢ ወደሚገኝ አዲስ እስር ቤት እንዲዘዋወሩ መደረጉን የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባው ሪፖርተራችን ዘግቧል።
የታሳሪ ቤተሰቦችን እና ጠበቆችን ያነጋገረው ሪፖርተራችን እንደ ገለጸው ከሆኑ ተጠርጣሪ ፖለቲከኞቹ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዲወጡ የተደረገው በእስር ቤቱ ብዙ ታሳሪዎች መኖራቸውን ተከትሎ ከእነርሱ እስር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ የጠያቂ መጨናነቅ መፈጠሩ በጸጥታ አባላቱ ዘንድ ስጋት በመፍጠሩ ነው።
እስረኛ ፖለቲከኞቹ ዛሬ እንዲዘዋወሩበት የተደረገው ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘው ትልቅ ግቢ ቀደም ሲል የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር፣ የሰላም ሚኒስትር መ/ቤቶች በመሆን ከዚህ ቀደም በተለያዮ ጊዜያት አገልግሏል።
ይህን ግቢ መንግሥት ለወራት ዘግቶት ውስጡን ሲያድሰውና በተለየ መንገድ ሲያንጸው እንደነበር የሚናገሩት ታማኝ የዜና ምንጮች አሁን ላይ ይህ ግንባታ በመጠናቀቁ መንግሥት በልዮ ሁኔታ የሚያስራቸውን ግለሰቦች በቀጣይም በዚህ አዲስ ስፍራ ሊያስቀምጣቸው እንደሚችል ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተያዘበት ወቅት በጸጥታ ኃይሎች ድብደባ የተፈጸመበት እስክንድር ነጋ ከአንድ ሳምንት በላይ ታስሮበት በነበረው ሁለት በሁለት ከሆነ ጠባብ ክፍል ከጥቂናት ቀናት በፊት ወደ ሌላ ሦስት በሦስት ወደሆነ ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ ለብቻው እንዲታሰር ተደርጎ እንደነበር ለመረዳት ችሏል።