ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ቀደም ሲል ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ መንገደኞች በ72 ሰዓታት ውስጥ ተመርምረው ከኮቪድ ነፃ መሆናቸውን ማረጋገጫ እንዲያመጡ ያስገድድ የነበረው መመሪያ ተሻሻለ።
የተሻሻለው መመሪያ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት መንገደኞች በአምስት ቀናት ውስጥ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንዲያቀርቡ ፍቃድ ይሰጣል።
በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታና ቀጣይ አዝማሚያ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ጥልቅ ውይይት ያካህሄደው የሚኒስትሮች ኮሚቴ፤ አስቀድሞ የወጣው በ72 ሰዐት የምርመራ ወረቀት እንዲቀርብና ለ14 ቀናት በቤት ውስጥ ለይቶ የማቆየት አስገዳጅ መመሪያ እንዲሻሻል ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
በመጀመሪያው መመሪያ ከውጪ የሚመጡ ዜጎች የምርመራ ውጤት ካልያዙ ለሠባት ቀን ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እንደሚደረግም አይዘነጋም።
መንገደኞች ባሉበት አገር ተመርምረው ውጤታቸውን ይዘው ኢትዮጵያ እስከሚገቡ ከሦስት ቀናት በላይ ይወስድብናል የሚል ቅሬታ ከተለያዩ መንገደኞች መምጣቱን ተከትሎ ማሻሻያ መደረጉን ያስታወሱት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፤ በአንድ በኩል ውጤቱ በጣም ከቆየ ያንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እና የመከላከል ሥራውን በማያደናቅፍ ሁኔታ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ እንደተገኘም ተናግረዋል።