የተባበሩት መንግሥታት ኮሮናን ለመከላከል ከፍተኛ የተባለውን ገንዘብ ጠየቀ

የተባበሩት መንግሥታት ኮሮናን ለመከላከል ከፍተኛ የተባለውን ገንዘብ ጠየቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የተባበሩት መንግሥታት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችለውን ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቁ ተነገረ።

ተቋሙ እስካሁን ከነበረው ከፍተኛ ገንዘብ የተጠየቀበት የገንዘብ መጠን 10.3 ቢሊየን ዶላር መሆኑ ታውቋል።
ዓለም ላይ ወረርሽኙ ባስከተለው ተፅዕኖ ሳቢያ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ወደ 265 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች ለርሃብ ሊጋለጡ ስለሚችሉ የሚሰበሰበው ገንዘብ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውንና በዚህ የተጎዱ አገራትን ለመደገፍ እንደሚውል ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።
 በፍጥነት እርምጃ ካልተወሰደ በስተቀር የዐሥርተ ዓማታትን እድገት ወደኋላ እንደሚመልስ ያስጠነቀቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤  ወረርሽኙ መስፋፋት በጀመረበት መጋቢት ወር ላይ 2 ቢሊየን ዶላር ገንዘብ መጠየቁን አስታውሶ፤ አሁን የተሻሻለው የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄም ከፍተኛ ቢሆንም፤ ሃብታም አገራት የፋይናንስ ሕጋቸውን ወደ ኋላ አድርገው ለደሃ አገራት ድጋፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲል አሳስቧል።
ሀገራቱ ይህን ልገሳ ካላደረጉ ግን ሚሊየኖች ለርሃብ እንደሚጋለጡና ዓለም ከፍተኛ የሆነ ቀውስ እንደሚገጥማት ድርጅቱ እወቁልኝ ብሏል። “በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኛ ሠራተኞች በእንቅስቃሴ ገደቡ ምክንያት ሥራ እየሠሩ ባለመሆናቸው ወደ አገራቸው ገንዘብ መላክ አይችሉም። ለህፃናት የሚሰጡ የክትባት ፕሮግራሞችም ቆመዋል። ለዓመታት በግጭት ውስጥ ያሉ አገራትም ኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም የላቸውም” ያለው የተባበሩት መንግሥታት የመንን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በቀጣይ ከፍተኛ የሆነ የሞት ደመና ማንዣበቡን ገልጿል።

LEAVE A REPLY