ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢትዮጵያ ውስጥ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት 4 ነጥብ 4 ሚሊየን የከተማ መኖሪያ ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ መያዙ ተነገረ።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ይህንን ቢልም የዘርፉ ምሁራን በበኩላቸው፤ የሚገነቡ ቤቶች ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ለነዋሪዎች መቅረብ እንዲችሉ የከተማ ፕላንና የተደራጀ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ሲሉ ምክር ለግሰዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የከተማ ልማት ዘርፍ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድን ለዘርፉ ባለሙያዎች አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል። በመሪ የልማት ዕቅዱ ለከተማ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የመኖሪያ ቤትና መሰረተ ልማት ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ሚኒስትሯ አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ከ24 ሚሊየን በላይ መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ አይሻ “እስከ 2022 ዓ.ም ቁጥሩን ወደ 40 ሚሊየን በማሳደግ 35 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የከተማ ነዋሪ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ከተሞች የሚነሳውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ኢ-ፍትሃዊነትና የጥራት ችግር ለማሻሻል በመንግሥት፣ በባለሃብቶች፣ በማህበራትና በሌሎችም መንገዶች 4 ነጥብ 4 ሚሊየን መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ መያዙ ተገልጿል።
በከተሞች የቤት ባለቤትነት ላይ ሁሌም ቢሆን ተቃውሞ እንደሚቀርብ እየተነሳ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በመሪ የልማት ዕቅዱ የተገልጋዮችን እርካታ 80 በመቶ ለማድረስ እንሠራለን ካሉ በኋላ፣ በከተሞች የድህነት ምጣኔን ከ15 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ በማድረግ የከተሞች ምርት የሀገራዊውን ጥቅል ኢኮኖሚ 73 በመቶ ለመሸፈን ውጥን መያዙን አስረድተዋል።