የኦነግ ባለሥልጣናት የታሰሩበት ቦታ ፈጽሞ ለማወቅ እንዳልተቻለ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ አደረገ

የኦነግ ባለሥልጣናት የታሰሩበት ቦታ ፈጽሞ ለማወቅ እንዳልተቻለ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ አደረገ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በቅርቡ በቁጥጥር ስር የዋሉ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች ሰዎች ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲያሳውቅ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሺኅዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ያመላከተው ዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፤ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የት እንዳሉ በማይታወቁበት ሁኔታ ተለይተው ተይዘዋል ሲል መንግሥትን ከስሷል።
በዚህ ወቅት በቁጥጥር ሥር  ከዋሉት መካከል ጃዋር መሐመድና በቀለ ገርባ ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፣ እሰክንድር ነጋ ከባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ፣እንዲሁም ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ዋነኛ የተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንደሚገኙበት አምንስቲ በመግለጫው አስታውሷል።
ባለሥልጣናት ታሳሪዎቹ ያሉበትን ቦታ ለቤተሰቦቻቸው ባለማሳወቃቸው ጭንቀትን እየፈጠሩ ናቸው ያሉት የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ  የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ሓላፊ ዲፕሮስ ሙቼና፤ “በአስቸኳይ ያሉበትን ቦታ በማሳወቅ ክስ እንዲመሰርቱባቸው ካልሆነም በአስቸኳይ እንዲለቀቁ” ሲሉ የኢትዮጵያን መንግሥት ጠይቀዋል።
 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አሳሳቢ በሆነበት በዚህ ወቅት ተጠርጣሪዎቹ ንጽህናቸው ባልተጠበቁና በተጨናነቁ ሁኔታዎች ውስጥ ሊታሰሩ ይችላሉ በሚል የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ጭንቀት ውስጥ ላይ መውደቃቸውን መግለጫው ያሳያል።
የታሰሩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ዋነኛ ባለሥልጣናት የት እንዳሉ ለማወቅ እንዳልቻሉ ጠበቆቻቸውን በመጥቀስ መረጃውን ይፋ ያደረገው አምንስቲ ፤ የፌደራል፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖችን ጨምሮ ግለሰቦቹ በእነሱ ቁጥጥር ስር እንዳልሆኑ መግለጻቸውንም ይፋ አድርጓል።
“ግለሰቦችን በእስር ለማቆየት የሚቻለው ፖሊስ በታሳሪዎቹ ላይ ጠንካራ ማስረጃ ካለው ብቻ ነው። ከዚህ ውጪ ፖሊስ ማስረጃ በሚያፈላልግበት ጊዜ ሰዎች የነጻነት መብታቸው ተገፎ ሊታሰሩ አይገባም”  ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ወደተለመደው የጭቆና መንገድ መመለስ የለባቸውም። የመቃወምና የተለየ የፖለቲካ ሀሳብ ማራመድን መብት ማክበር ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።

LEAVE A REPLY