ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አሁን ያለው የዝናብ ሁኔታ የህዳሴ ግድቡን በውሃ ለመሙላት አመቺ መሆኑን ተከትሎ በመጀመሪያው ዓመት ለመሙላት የታቀደው የውሃ መጠን ሞልቶ በግድቡ አናት ላይ እየፈሰሰ መሆኑ ተነገረ።
በዚህ ዝናባማ ወር ውስጥ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በነበረው መልካም የዝናብ ሁኔታ በመጀመሪያው ዓመት ለመሙላት የታቀደው የውሃ መጠን ሞልቶ፤ ውሃው በግድቡ አናት ላይ እየፈሰሰ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ላይ ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የግድቡ የውሃ ሙሌት ሐምሌ አጋማሽ ላይ እንደሚጀምር ቁርጠኝነቱን ሲያሳውቅ ቆይቷል። ይህን ተከትሎም ሐምሌ 5 ቀን የግድቡ ውሃ መሞላት መጀመሩን የሳተላይት ምስሎችን ማስረጃ ማስረጃ ያደረጉ የተለያዮ ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ቢዘግቡም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ጉዳይን አድበስብሶ ለማለፍ መሞከሩ ይታወሳል።
ግብጽ እና ሱዳን በበኩላቸው በግድቡ ዙሪያ ሙሉ ስምምነት ሳይደረስ ውሃ መሙላት መጀመር ለድርድር ሂደት እክል ይሆናል እያሉ ሲያስጠነቅቁ ከርመዋል።
የሦስቱ አገራት መሪዎች እና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሰብሳቢ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ የሚመሩት ውይይት አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቦ መጠናቀቁ አሁን ላይ እየተነገረ ነው።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በቴክኒካል ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ውይይቶችን በማድረግ አጠቃላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ መሰማማታቸው የተነገረ ሲሆን፤ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳም የተካሄደው ውይይት ውጤታማ እንደነበረ ጠቁመው፣ የሦስቱ አገራት ውይይት ይቀጥላል ካሉ በኋላ፤ የአፍሪካዊያንን ችግር በአፍሪካ መፍትኄ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት በስበሰባው የተሳተፉትን አካላት አመስግነዋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንሰትር አብደላ ሃምዱክ በበኩላቸው የተደረገው ውይይት ስኬታማ እንደነበረ አስታውሰው የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር ግድቡ የሚሞላበትን እና የሥራው ሂደት በተመለከተ ድርድሮች እንዲቀጥሉ ተግባብተናል ሲሉ ተናግረዋል።
የፕሬዝደንት አል-ሲሲን ቢሮ ጠቅሶ የዘገበው አሃረም ኦላይን ግብጽ ከኢትዮጵያ እና ከሱዳን ጋር ግድቡ የሚሞላበት እና የግድቡን አሠራር በተመለከተ ከስምምነት ለመድረስ ተስማምታለች ብሏል።