ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሰኔ ወር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በህገ-ወጥ ንግድ ሲዘዋወሩ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ የተለያዮ ዕቃዎች መሀል የተለያዩ ዓይነት ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች በቀዳሚነት ተቀመጡ።
በህግ ከለላ በቁጥጥር ሥር የዋለው የኮንትሮባንድ እቃ ግምታዊ ዋጋው ባለፈው ዓመት ከተያዘው 800 ሚሊየን ብር ግምት ብልጫ እንዳለው ተነግሮለታል።
በበጀት ዓመቱ ከ2.4 ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ ቁሶች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ያሳወቀው ነገቢዎች ሚኒስትር፤ ከዚህ መካከል 2.14 ቢሊየን ብር የሚገመት ዋጋ ያላቸው እቃዎች የተያዙት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሃገር ሊገቡ ታስቦ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት ነው ብሏል።
ከህግ ውጭ ወደ ሀገር ሊገቡ ሲሉ ተይዘዋል ከተባሉት መካከልም በ2012 በጀት ዓመት ከፍተኛውን ቁጥር የያዘው ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እንደሆነ የጠቆመው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ አዳዲስ አልባሳት እና አደንዛዥ እፅ በሁለተኛና የሦስተኛ ደረጃን መቀመጣቸውን አስረድቷል።
ከ2.4 ቢሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ አላቸው ከተባሉ የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል፤ ከ293 ?ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተያዙት በህገወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በተጠቀሰው መንገድ ሊወጡ ሲሉ ከተያዙት መካከል ደግሞ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር የመጀመሪውን ደረጃ ይይዛል የተባለ ሲሆን፣ አደንዛዥ እፅና የግብርና ምርቶች ከህግ ውጭ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ ከተያዙት ቁሳቁሶች ውስጥ 2ኛና 3ኛ ደረጃን ይዘዋል።
አቃቂ ቃሊቲ፣ አዲስ አበባ ኤርፖርትና ጅግጅጋ ከፍተኛ የገቢ ኮንትሮባንድ የተያዘባቸው የጉምሩክ ቅርንጫፎች ሆነው መመዝገባቸውን ያመላከተው መረጃ፤ የዘንድሮ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችና የገንዘብ ዝውውሩን ጨምሮ የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተከወነው ሥራ የህይወትን መስዋዕትነት ማስከፈሉንም ይፋ አድርጓል።