ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በዱከም ከተማ ውስጥ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ በኮሮና ቫይረስ በተያዘ ግለሰብ በቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙ 44 ሰዎች በኮሮናቫይረሰ መያዛቸው ታወቀ።
ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሆኑት ከአርባ በላይ ሰዎች መካከል በሐዘን ላይ ያሉ የሟች የቤተሰብ አባላትን እንደሚጨምር የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሓላፊ አቶ ደረጄ አብደና አረጋግጠዋል።
ለወረርሽኙ መተላለፍ ምክንያት የሆነው ግለሰብ ሕይወቱ ያለፈው ባለፈው ሳምንት ባጋጠመው የመኪና አደጋ ቢሆንም በአስክሬኑ ላይ በተደረገ ምርመራ የኮሮናቫይረስ እንደነበረበት ሊታወቅ ችሏል።
በትራፊክ አደጋ የሞተው ወጣት የምርመራ ውጤቱ ከመታወቁ በፊት አስከሬኑ ለቤተሰብ ተሰጥቶ አስፈላጊው ዝግጅትና ሥነ ሥርዓት ተከናውኖ እንዲቀበር ከተደረገ በኋላ ሟች አስከሬን ላይ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱ በቀብሩ ላይ የታደሙ ሰዎችን ክፉኛ አስደንግጧል።
የሟች ቤተሰብ አባላት፣ ጎረቤቶች እና በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙና ንክኪ ሊኖራቸው ይችላል የተባሉ ሰዎችን የመለየት እና ምርመራ የማድረግ ሥራዎች ሲከናወኑ እንደቆዩ ተሰምቷል።
ይህን ተከትሎ እስከ ሰኞ ድረስ በንክኪ ምክንያት ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ በተባሉ ሰዎች ላይ በተደረገው ልየታና ምርመራ መሠረት በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 44 መድረሱን አቶ ደረጄ አብደና ይፋ አድርገዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ሓላፊ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሕይወታቸው ላለፉ ሰዎች በሚከናወን የቀብር ሥነ ሥርዓቶች አማካይነት የሚከሰተው የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ለበሽታው መዛመት አመቺ አጋጣሚዎች እየሆኑ እንደመጡም ተናግረዋል።
በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸው ካለፉ ሰዎች አስከሬን ጋር ከሚደረግ የቀጥታም ሆነ የተዘዋዋሪ ንክኪ ባሻገር በቀብር ሥነ ሥርዓቶች ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ስለሚገኙ ከሐዘኑ ታዳሚ ጋር በሚኖረው መቀራረብ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ለመተላለፍ እድል እንደሚያገኝ ነው የተነገረው።
ከዚህ ሌላ በቀብር ሥነ ሥርዓትና በማስተዛዘን ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች የሚታደሙ ከመሆናቸው ባሻገር፤ ርቀትን መጠበቅና የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም አምብዛም ስለሆነ ለቫይረሱ የመጋለጥ እድልን ከፍ እያደረገ እንደሆነ ሓላፊው አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በጉጂ ዞን፣ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወረዳ እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ አካባቢ በጥንቃቄ በጎደለው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የተሳተፉ በርካታ ሰዎች ለኮሮናቫይረስ መጋለጣቸውን ኢትዮጵያ ነገ መዘገቡ ይታወሳል።