ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኤርትራ ከፍተኛ የጦር ሠራዊትና የደኅንነት አመራር አባላት ልዑካን ቡድን ወደ ሱዳን መጓዛቸውና ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸው አነጋጋሪ ሆኗል ተባለ።
እስካሁን ድረስ ዝርዝር ማብራሪያ ያልተሰጠበት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጉብኝትና የኤርትራ ጉዞ ማግስት ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ከፍተኛ የወታደራዊና የደህንነት ሹሞቻቸውን ወደ ሱዳን መላካቸው ምን የታቀደ ነገር ይሆን? የሚል ጥያቄን አስነስቷል።
የኤርትራው ከፍተኛ ወታደራዊ የልዑካን ቡድን በአገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በጀነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ የሚመራ ሲሆን፤ የማዕከላዊ ዞን አዛዡ ሜጀር ጀነራል ሮሞዳን አወሊያ፣ የባሕር ኃይል አዛዡ ሜጀር ጀነራል ሁመድ ካርኬሪ እና የብሔራዊ ደኅንነት ሓላፊው ብርጋዴር ጀነራል ብረሀ ካሳ እንደሚገኙበትም ታውቋል።
የልዑካን ቡድኑ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተላከ መልዕክትን ለሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ ለሆኑት ሉቴናንት ጄነራል አብዱል ፋታህ አል-ቡርሃን አብዱል ራህማን እንዳቀረበ የሱዳን የዜና አውታሮች ዘግበዋል።
ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ የተላከውን መልዕክት ለሱዳን ምክር ቤት ሊቀመንበር ያቀረቡትና የኤርትራን ልዑካን ቡድንን የመሩት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ መሆናቸውን የተናገረው ቢቢሲ በሥነ ሥርዓቱ ላይ በካርቱም የኤርትራ አምባሳደርን ጨምሮ የሱዳን ከፍተኛ የደኅንነትና የሠራዊት አመራሮች ተገኝተዋል ሲል አስታውቋል።
የሱዳን የሽግግር አስተዳደር ሊቀ መንበር አል-ቡርሃን ፤ የሁለቱ አገራት ሠራዊት አመራሮች የሕዝባቸውን ፍላጎት ለማሟላት በወታደራዊውም ሆነ በደኅንነት ዘርፎች ያለውን ግንኙነቱን ለማጠናከር መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም እንዳለባቸው የተናገሩ ሲሆን፤ ጀነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስና ልዑካን ቡድናቸው ከሱዳኑ የጦር ኃይሉ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጀነራል ሞሐመድ ኦስማን አል-ሁሴን እንዲሁም ከሱዳን የደኅንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ ጋር ምስጢራዊ ውይይት እንዳደረጉ እየተነገረ ነው።
የኤርትራ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ለቀናት የሚቆይ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ሱዳን መሄዳቸው የተነገረ ሲሆን በዋናነት በሁለቱ አገራት ስላለው ወታደራዊና የደኅንነት ሁኔታዎች ላይ እንደሚወያዩ የተለያዮ ምንጮች ቢናገሩም ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።