የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በኹከቱ ከአንድ ቪኅ በላይ መኖሪያና ንግድ ቤቶች መውደማቸውን አመነ

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በኹከቱ ከአንድ ቪኅ በላይ መኖሪያና ንግድ ቤቶች መውደማቸውን አመነ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተለያዮ የኦሮሚያ ዞኖች በተነሳው ኹከት ከአንድ ሺኅ በላይ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ሱቆች መውደማቸው ተረጋገጠ።

የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ  መንግሥት በመኖሪያ ቤቶች፣ በንግድ ቤቶች እና በመንግሥት ተቋማት ላይ የደረሱትን ጉዳቶች፤ “የተቃጠሉ፣ የተሰባበሩ እና የተዘረፉ” በሚሉ ጎራዎች ከፋፍሎ የደረሰውን የጉዳት እያጠና ይገኛል ብለዋል።
እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋገት በቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ሲሆን፤ የአርቲስቱ ግድያ ከተሰማ በኋላ በአሮሚያ ክልል፤ 523 መኖሪያ ቤቶች የተቃጠሉ ሲሆን፣ 499 መኖሪያ ቤቶች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተሰባበሩ ማረጋገጥ ተችሏል።
በንግድ ቤቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት በአሃዝ ሲቀመጥ፤ 195 ሆቴሎች መቃጠላቸውን እና ሌሎች 32 ሆቴሎች ደግሞ በንብረት ላይ የመሰባበር ጉዳት መድረሱን ቃል አቀባዮ ተናግረዋልተናግረዋል። በተጨማሪም 104 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የቃጠሎ ውድመት እንደደረሰባቸው የክልሉ ባለሥልጣን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ስድስት አነስተኛ እና ግዙፍ ፋብሪካዎች በሁከቱ መቃጠላቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ የተቃጠሉ አነስተኛ ንግድ ቤቶች ቁጥር  232፣ እንዲሁም የተሰባበሩት አስተኛ ንግድ ቤቶች አሃዝ 219 መሆኑን ገልጸዋል።
ከሃጫሉ ግድያ በኋላ በተከሰተ ሁከት ከፍተኛ የንብረት ውድመት ከተከሰተባቸው ስፍራዎች መካከል ሻሸመኔ ከተማ አንዷ ስትሆን በዚህ ስፍራ 232 የግል እንዲሁም 12 የመንግሥት ተሸከርካሪዎች በእሳት እንዲጋዩ መደረጉ ተሰምቷል።
በጥቅሉ በኹከቱ በግል እና በመንግሥት ቤቶች እንዲሁም ተሽከርካሪዎች ላይ የደረሰው ጉዳት መጠን እየተጣራ መሆኑን  የተናገሩት ቃል አቀባዮ፤ ዘረፋን በተመለከተ ግን የተሰባሰቡ ማስረጃዎች ተጠናቅረው ስላላለቁ ዝርፊያ የተፈጸመበትን የንብረት መጠን ማወቅ ለጊዜው አዳጋች ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
በሰው እና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰው በምዕራብ አርሲ ሦስት ወራዳዎች ውስጥ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በተለይ በሻሸመኔ እና ባቱ ከተሞች እንዲሁም በባሌ ዞን ሮቤ እና አጋርፋ ከተሞች የደረሰው ጉዳት ከሌሎች አካባቢዎች አንጻር ከፍተኛ እንደሆነም አምነዋል።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትም ይሁን የፌደራል መንግሥቱ በወደሙ ቤት ንብረቶችና በጠፋ የሰው ሕይወት ላይ አኃዛዊ መረጃዎችን ይፋ ቢያደርግም ከደረሰው አስከፊ አደጋ አኳያ ቁጥሩ አነስተኛ ሆኖ የቀረበና ከእውነታው የሚጣረስ መሆኑን ጉዳቱ የደረሰባቸው የተለያዮ ወገኖች ይናገራሉ።

LEAVE A REPLY