የጥላቻ ንግግሮችን የሚያሰራጩን የሚቆጣጠር “ተጋምደናል” የተሰኘ ኔትዎርክ ተቋቋመ

የጥላቻ ንግግሮችን የሚያሰራጩን የሚቆጣጠር “ተጋምደናል” የተሰኘ ኔትዎርክ ተቋቋመ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሱ የመጡት በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች መደበኛ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሰራጩ ጥላቻንና ጥቃትን የሚያበረታቱ መልዕክቶችን  ለማስቆም የሚያስችል ኔትዎርክ መቋቋሙ ተሰማ።

የጥላቻ መልዕክቶች በኢትዮጵያ እየታየ ላለው መጠፋፋት አስተዋጽኦ እንዳላቸው ያመኑ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ናቸው ጥፋቱን ለማስቆም  መላ የዘየዱት።
  በአሜሪካ የሚኖሩት የዚህ እንቅስቃሴ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ነአምን ዘለቀ (የቀድሞ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ከፍተኛ አመራር) ፤  ኔትዎርኩ በተለያዩ ዘርፎች የተዋቀሩ ኮሚቴዎች ያሉት እንደሆነና፤  የሕግ፣ የሚዲያና ዲፕሎማሲ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ የተዋቀረ አደረጃጀት እንደሆነም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አማራጭ ኔትዎርኩ በአሜሪካ፣ በካናዳና በአውሮፓ ሀገራት ውስጥ ያሉ በርካታ የፖለቲካ ሰዎች፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፣ ሲቪክ ማኅበረቦች የተሰባሰቡበት እንደሆነም  ጨምረው አስታውቀዋል።
ኔትወርኩ በአገር ውስጥ መረጋጋት እንዲመጣ ፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፤ ወንጀለኞችና ሓላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ለሕግ እንዲቀርቡ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም በማብራሪያቸው ላይ ጠቁመዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያው ኮሚቴ “ተጋምደናል” በሚል መርህ የማኅበራዊ ሚዲያ ኮሚቴው (Interunited)  ዘመቻውን የጀመረ ሲሆን፤ የጥላቻ ንግግሮችን በመሰብሰብና ሪፖርት ከማድረግ ባሻገር ባሉት ገፆች አማካይነትም መልዕክቶችን የማስተላለፍ ሥራ እየተሠራ መሆኑ ታውቋል።
የተዋቀረው የሕግ ኮሚቴው እንዲህ ዓይነት መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃንና ግለሰቦች ባሉበት ሀገር ውስጥ ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ ለሕግም እንዲቀርቡ የሚሠራ ሲሆን ፤ መረጃዎችን በመሰብሰብ በማደራጀት የሚሠራው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቡድኑ የሚደገፍ መሆኑ ተነግሮለታል።
እስካሁንም በኔትወርኩ በተከፈተው የኢሜል አድራሻ በርካታ ማስረጃዎች እየደረሷቸው መሆኑን የጠቆሙት ነአመን ዘለቀ፤ “በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም በተለያዩ የዓለም 0ቀፍ ሚዲያዎች በተዛባ መልኩ ዘገባዎች የተሠሩ በመሆኑ ፤ የሚዲያና ዲፕሎማሲ ኮሚቴው ማስረጃዎችን በማሰባሰብ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲደረጉ እየየተሠራ ነው” ብለዋል።
መቀመጫቸውን ከሀገር ውጪ አድርገው በሕዝቡ ውስጥ መረጋጋትና ሰላም እንዳይኖር፤ ከባድ የጥላቻና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ናቸው የሚባሉት አካላት በአንድ ወገን ያሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ የተለያዩ ብሔሮችን እንወክላለን የሚሉ እንደሆኑ አስተባባሪው  ይፋ አድርገዋል።

LEAVE A REPLY