ለሦስት ሳምንታት የተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ዛሬ መለቀቁ ታወቀ

ለሦስት ሳምንታት የተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ዛሬ መለቀቁ ታወቀ

Business concept vector illustration.

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ለሦስት ሳምንታት ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች መለቀቁ ተሰማ።

የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በመላ ኦሮሚያና በአዲስ አበባ የተወሰኑ ሥፍራዎች ላይ ከፍተኛ ኹከት የፈጠሩ የተደራጁ ቡድኖችና የመንጋዎችን እንቅስቃሴ ተከትሎ መንግሥት የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመዝጋት መገደዱን መግለጹ አይዘነጋም።

የነበረውን ነውጥ በተወሰነ ደረጃ መቆጣጠር መቻሉን ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የዋይፋይ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲመለስ ቢደረግም፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ተጠቃሚ ያለው የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት እስከ ትናንት ዝግ ሆኖ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ እንደዋነኛ ምክንያት የጠቀሰው አንዳንድ ወገኖች ግጭትና አለመረጋጋትን የሚያባብሱ የጥላቻ መልዕክቶችን ለማሰራጨት መጠቀማቸውን ነው።
 የኢንተርኔት አገልግሎት የብሔር ጥላቻን ለማስፋፋት ጥቅም ላይ በመዋሉ መንግሥት አገሪቱንና ሕዝቡን የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ለማቋረጥ ተገዶ ነበር ያሉት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት የሆኑት ቢልለኔ ስዮም ነገሮች ሲስተካከሉ ደግሞ የተቋረጠውን አገልግሎት መመለስ ደግሞ የመንግሥት ግዴታ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ግንባታ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ዛዲግ አብረሃ በበኩላቸው ኢንተርኔት በአንዳንድ ወገኖች ለጥላቻ ንግግር ማሰራጫ መሣሪያ እንደተደረገ ጠቁመው፤ በብሔሮችና በሃይማኖቶች መካከል ግጭቶች እንዲቀሰቀስ መሣሪያ በመሆኑ እንዲቋረጥ ተደርጓል ብለዋል።
“መምረጥ የነበረብን ከመረጃ ነጻ ፍሰትንና የሕዝባችን ሕይወት ከመካከል ነበር፤ በዚህም ለሰው ልጅ ሕይወት ቅድሚያ ሰጥተናል” ያሉት አቶ ዛዲግ አብርሃ የተወሰደው እርምጃ የዜጎችን ደኅንነት ከመጠበቅ አንጻር መሆኑን አስታውቀዋል።
መደበኛ ሥራቸው ኢንተርኔት መሰረት ላይ ያደረጉ በርካታ ተቋማት ባለፉት ሦስት ሳምንታት ከፍተኛ መጠን ያለው ገቢ ማጣታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል። ዛሬ የተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ወደ መደበኛ ሥርጭት መመለሱ የተባለውን ችግር ይቀርፈዋል ተብሎ ቢታመንም በኹከቱ ወቅት በመንጋዎች የተፈጸመው ዘግናኝ እና አሳፋሪ፣ ብሔርና  ሃይማኖት ተኮር ጥቃትን የሚያሳዮ ምስሎች እንደ አዲስ እየተለቀቁ በሕዝብ ዘንድ ቂም በቀል ሊያስቋጥር የሚችል እድል ይፈጥራል የሚል ስጋትን በብዙዎች ዘንድ ፈጥሯል።

LEAVE A REPLY