ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉና ለግጭት የሚዳርጉ መልዕክቶችን በሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወሰደው እርምጃ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን አስታወቀ።
ባለሥልጣኑ የአገርን ሠላምና የሕዝብን አንድነት የሚሸረሽሩ መገናኛ ብዙኃን ከእንግዲህ በኋላ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ኮስተር ያለ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
መገናኛ ብዙኃኑ ለዓመታት ከነበሩበት ጫና ወጥተው በነጻነት እንዲዘግቡ፣ የሕዝቡን ሐሳብ እንዲያስተላልፉና ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ያስታወሱት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዷለም፤ ይሁን እንጂ ይህን ነጻነት በአግባቡ የማይጠቀሙና የጋዜጠኝነትን ስነ-ምግባር የሚጥሱ መገናኛ ብዙኃን ተፈጥረዋል ብለዋል።
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ሽፋን በማድረግ የዜጎችን ሠላምና አብሮነት የሚሸረሽሩ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ የነበሩት ኦ.ኤም.ኤን እና ድምፀ ወያኔ ጣቢያዎች መታገዳቸውን፣ የትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያም ስርጭቱ እንዲቋረጥ በመንግስት እርምጃ እንደተወሰደበት ያስታወሱት ሓላፊው፤ ሰላም ለማስከበር ከወሰደው እርምጃ ጎን ለጎን መገናኛ ብዙኃኑን ተጠያቂ በማድረግ ረገድ ባለሥልጣኑ አዋጁ በሚፈቅድለት ሕግና ደንብ መሠረት ኃላፊነቱን የሚወጣበትና የማይታገስበት ጊዜ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
“መገናኛ ብዙኃን ድንጋይ መወራወሪያ ሳይሆን ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሀሳቦች የሚፋጩባቸውና ሀሳብ የሚያሸንፍባቸው ሊሆኑ ይገባልም” ያሉት አቶ ወንድወሰን አንዷለም፤ “ሕዝቡ እውነተኛና ትክክለኛ መረጃ እንዲኖረው ከማድረግ ይልቅ መቃቃርን የሚሰብኩ የመገናኛ ብዙኃን አሁንም መኖራቸውን ባለሥልጣኑ ታዝቧል። ስለሆነም የአንድ ወገንና ቡድንን ፍላጎት በሚያንጸባርቁ፣ የተቋቋሙበትን ዓላማ በሚዘነጉ መገናኛ ብዙኃን ላይ አሁንም የእርምት እርምጃ የመውሰድ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉም ይፋ አድርገዋል።
የችግራቸው መጠን ቢለያይም የመፍትኄ አካል ከመሆን ይልቅ፣ የችግሩ አካል የመሆን አዝማሚያ በመገናኛ ብዙኃኑ እንደሚስተዋል ያመላከቱት አመራሩ፤ ይህንን ከመሠረቱ ለማስቀረት ባለሥልጣኑ ሕግን በማስከበር መገናኛ ብዙኃኑ በትክክለኛ መንገድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ እንደሚያደርግ ይፋ አድርገዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 72 የማኅበረሰብ፣ የግል ፣ የንግድ እና የሕዝብ ራዴዮ ጣቢያዎች እንዲሁም 37 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሕጋዊ ምዝገባ አካሂደው በሥራ ላይ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።