ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ አስታከው ለዘረፋና ለጥፋት በወጡ የመንጋ አባላት የተለያዮ ሁለት ከተሞች የሚገኙ ሪዞርቶቹ የወደመበት አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ዳግም ወደ ሥራ የመመለሱ ዕድል በእጅጉ የጠበበ መሆኑን ይፋ አደረገ።
ሀያ ሠባት ሪከርዶችን የሰባበረውና የኢትዮጵያ ምልክት የሆነው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፤ በተነሳው ኹከት በባቱ ወይም ዝዋይ እና በሻሸመኔ ከተሞች ባስገነባው ሪዞርት ለወደመበት ኢንቨስትመንት መንግሥት ድጋፍ ካደረገለት ብቻ ወደ ሥራው እንደሚመለስ አስታውቋል።
አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.1 ላይ እንደ ገለጸው የድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞትን ተከትሎ በባቱ (ዝዋይ) እና ሻሸመኔ ከተሞች በሥራ ላይ የነበሩት ሆቴሎች ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል።
ቀደም ሲል በእነዚህ ከተሞች የነበረውን ኢንቨስትመንት ማቋረጡን አትሌቱ ያሳወቀ ቢሆንም፤ አሁን ላይ መንግሥት ለወደመበት ንብረት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ካደረገለት ወደ ሥራ እንደሚመለስ አረጋግጧል።
የዝዋይ ከተማውን ሪዞርት ወደ ሥራ ለመመለስ ከአንድ ዓመት በላይ የጥገና ጊዜ የሚፈጅ ሲሆን፤ የሻሸመኔው “ኃይሌ ሪዞርት” ቅርንጫፍ ግን የግድ እንደ አዲስ መገንባት ስለሚጠይቅ ወደ ሥራ ለመመለስ በትንሹ ሦስት ዓመታትን እንደሚፈጅ የጠቆመው ያለመንግሥት ድጋፍ ሪዞሮቶቹን ዳግም የመገንባት ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል።