ጭላሎ ሆቴል 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረት እንደወደመበት ባለቤቱ አስታወቁ

ጭላሎ ሆቴል 3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ንብረት እንደወደመበት ባለቤቱ አስታወቁ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከተሠራ ዐራት ዐሥርተ ዓመታትን ያስቆጠረውና ከሦስት ሳምንት በፊት በኹከት ናፋቂ መንጋዎች ከፍተኛ ጥፋት የደረሰበት ጭላሎ ሆቴል ለ2.9 ሚሊዮን  ብር ኪሳራ እንደተጋለጠ  ታወቀ።

ከ 40 ዓመታት በፊት በድምፃዊ ሳራ ቲ አባት( በአቶ ታደሰ) እንደተቋቋመ የሚነገርለት የዝዋይ ከተማው ጭላሎ ሆቴል በሀገሪቱ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ከ2.9 ሚሊየን ብር በላይ ውድመት እንደደረሰበት የሆቴሉ ባለቤት ገልጸዋል።
በበርካታ ኢትዮጵያውያን የሻሸመኔ ድምቀት ተብሎ የሚጠራው እድሜ ጠገቡ  ጭላሎ ሆቴል በቅርቡ እድሳት ያደረገ ሲሆን፤ ከእድሳቱ በኋላ ከፍተኛ ወጪ ወቶባቸው የተገዙ ሶፋዎች፣ ወንበሮች እና በሆቴሉ የሚገኙ ልዩ ልዩ ንብረቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸው ተረጋግጧል።
የጭላሎ ሆቴል ባለቤት አቶ አዲስ ታደሰ በሆቴሉ የደረሰው አጠቃላይ ጉዳት ከ2.9 ሚሊየን ብር እንደሚያወጣ ጠቁመው፤ “ከሀገራችን እና ከተወለድንበት ከተማ የትም አንሄድም፤ ሆቴሉንም ዳግም እንሰራዋለን፤ ለዚህም መንግሥት እና የአካባቢው ማህበረሰብ ከጎናችን ሊቆም ይገባል” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መንግሥት የሀገሪቱን ሰላም እና ደህንነትን ማስከበር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባዋል ያሉት አቶ አዲስ ፤ ሆቴሉ ለ30 የከተማ ነዋሪዎች የሥራ እድል የፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜና 63 ዓመታት ያቆጠረውና በጎባ ከተማ የሚገኘው ይልማ 50 ሆቴል ሙሉ በሙሉ ውድሙን መረጃዎች አረጋግጠዋል።

LEAVE A REPLY