ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢዴፓ ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታወቀ።
ፖሊስ ልደቱ አያሌውን የያዛቸው በቅርቡ በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት በማስተባበርና በመደገፍ እንደሆነ አቶ አዳነ ታደሰ የኢዴፓ ፕሬዝዳንት ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ዛሬ ረፋድ ላይ አዲስ አበባ ውስጥ በፌደራል ፖሊስ እንደተያዙና ተላልፈው ለኦሮሚያ ፖሊስ አባላት መሰጠታቸውን ጭምጭምታውን ሰምቶ በእጅ ስልካቸው ላይ ለደወለው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢ የተናገሩት አቶ ልደቱ አያሌው ፖሊሶቹ በያዟቸው ወቅት ከሦስት ሳምንት በፊት በደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ በተፈጠረው ኹከት ላይ እጅህ አለበት በሚል የክልሉ መንግሥት ክስ እንደመሰረተባቸው የገለጹላቸው መሆኑን ለሪፖርተራችን አስረድተዋል።
“አሁን ወደ ደብረዘይት እየተወሰድኩ ነው፣ መጀመሪያ ላይ የያዙኝ የፌደራል ፖሊስ አባላት የነበሩ ቢሆንም ወዲያውኑ ለኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች አሳልፈው ሰጥተውኛል” በማለት በፖሊሶች ታጅበው ጉዞ ወደ ደብረ ዘይት ከተማ እያደረጉ ባለበት ወቅት በስልክ ለኢትዮጵያ ነገ የጠቆሙት ነባር ፖለቲከኛው ልደቱ አያሌው፤ ሰሞኑን በተለይም ከረቡዕ እለት ማለዳ አንስቶ በማያውቋቸው አካላት ከጧት እስከ ማታ ከፍተኛ ክትትል ይደረግባቸው እንደነበርና ከሁኔታው መክበድ አንጻር እስር ሊገጥማቸው እንደሚችል አስቀድመው መገመታቸውንም አስረድተዋል።
አቶ ልደቱ አያሌው ወደ ደብረዘይት ከተማ የተወሰዱት በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ክስ ስለተመሠረተባቸው ብቻ ሳይሆን፤ መኖሪያቸው ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የአሁኗ ቢሾፍቱ በቀደምቷ ደብረዘይት ከተማ ነው።
ከቢሾፍቱ ከተማ ፍርድ ቤት ልደቱን ለመያዝ ፖሊስ የመያዣ ትዕዛዝ ያወጣው ሐምሌ 03/2012 ዓ.ም (ከዐሥራ ዐራት ቀናት በፊት) መሆኑን የጠቆመው የኢትዮጵያ ነገ የአዲስ አበባ ዘጋቢ ፤ እስከ አሁን ድረስ ለምን ሳይያዙ እንደቀረ ለማድረግ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካለት አስታውቋል።