በኮንሶ ዞን በተከሰተ ግጭት 11 ሰዎች ሲሞቱ 21 ሺኅ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ታወቀ

በኮንሶ ዞን በተከሰተ ግጭት 11 ሰዎች ሲሞቱ 21 ሺኅ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ታወቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን እና በአሌ ልዩ ወረዳ መካከል በተነሳ የመሬት ይገባኛል ግጭት ቢያንስ የ11 ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ ከ21 ሺኅ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል ተባለ።

ግጭቱ የተከሰተው ከመሬት ይገባኛል ጋር ተያይዞ እንደሆነ ለቢቢሲ የተናገሩት የአሌ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ካራ ማሞ፤ ጥያቄው የቆየና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሁለቱ አካባቢ አስተዳደሮች መካከል ውይይት ሲደረግ እንደነበር ገልጸዋል።
የኮንሶ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሓላፊ አቶ ሀሰን ወላሎ፤  በአሌ ልዩ ወረዳ እና በኮንሶ ዞን ኮለኔ ክላስተር መካከል የደን መሬት እንደነበር በመናገር፣ የአሌ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ደኑን አላግባብ በመመንጠር ለመጠቀም መሞከራቸው ግጭቱ እንዲንቀሳቀስ መንስዔ ሆኗል ብለዋል።
ግጭቱ ከእሁድ ዕለት ጀምሮ የተቀሰቀሰ መሆኑን በመጥቀስም ቢያንስ የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እንዲሁም በዘጠኝ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰ የዞኑ ባለሥልጣናት ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ደረሰ የተባለው ግጭት በዋናነት የተቀሰቀሰው አሌ ልዩ ወረዳ እና ኮንሶ ዞን በሚዋሰኑበት “ኮለኔ ክላስተር “የነበረ ቢሆንም፤ ችግሩ አሁን ወደ ሌላ አዋሳኝ መንደር “ቱሩ ክላስተር ” ተስፋፍቶ ከ20 ሺኅ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንም አቶ ሀሰን በማብራሪያቸው አስታውቀዋል።
 በኮለኔ ክላስተር ይኖሩ የነበሩ 15 ሺኅ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ፣ እንዲሁም በቱሩ ክላስተር ላይ ደግሞ ይኖሩ የነበሩ ከ6 ሺኅ በላይ ነዋሪዎች እንደተፈናቀሉ ተሰምቷል።
ግጭቱን ተከትሎ በኮንሶ በኩል በእነዚህ ክላስተሮች ሥር ያሉ አራት መንደሮች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቤቶች በእሳት የተቃጠሉ ሲሆን፤ ሁለት መንደሮች ደግሞ ሙሉ በሙሉ፣ ሁለቱ ደግሞ በከፊል መውደማቸውን ሓላፊዎቹ አብራርተዋል።
ግጭቱ ያልታሰበ  እንደነበር የገለጹት አቶ ሀሰን፤ የዞኑ የፀጥታ ኃይልም ሆነ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ለመቆጣጠር ቢሞክርም አቅጣጫ በመቀያየርና በሦስትና በአራት የተለያዩ ቦታዎች ግጭቱ በመካሄዱ ለመቆጣጠር ፈታኝ ነበር ሲሉም ተናግረዋል።
የአሌ ልዩ ወረዳ እና በኮንሶ ዞን ተጎራባች ቀበሌዎች መካከል ያለውን ችግር በሰላማዊ ወይይት ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈውበት በተደጋጋሚ ሙከራ ቢደረግም ነገር ግን መግባባት ላይ ሊደረስ አለመቻሉ ታውቋል።

LEAVE A REPLY