ሁለት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑና የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ወጣቶች ዋስትና ተፈቀደላቸው

ሁለት የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑና የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ወጣቶች ዋስትና ተፈቀደላቸው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከሦስት ሳምንት በፊት ተከስቶ ከነበረው ኹከትና ጥቃት ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሁለት የአሜሪካ ዜጎች የዋስ መብት እንደተፈቀደላቸው ተሰማ።

ከሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተፈጠረው የመንጋ ጥቃት ላይ ተሳትፈዋል በሚል ከተጠረጠሩት ሠባት ሺኅ ሰዎች መሀል ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ ሦስት የአሜሪካ ዜጎች ይገኙበታል።
 የአሜሪካ ዜግነት አላቸው ከተባሉት ተጠርጣሪዎች መካከል ትናንት ፍርድ ቤት የቀረቡት ሬድዋን አማን እና ዩሱፍ በሽር የተባሉ ( የኦሮሞ ማኅበረሰብ ተወላጅ የነበሩና ዜግነታቸውን የቀየሩ) የዋስ መብታቸው እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤት መወሰኑ ተረጋግጧል።
ሬድዋን አማን እና ዩሱፍ በሽር ነዋሪነታቸው በአሜሪካ አገር የነበረ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚንሰትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ለቢቢሲ የጠቆሙት ጠበቃቸው አቶ ከድር ቡሎ፤  ሁለቱ ግለሰቦች አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው በ6ሺኅ ብር የዋስትና መብት ከእስር እንዲወጡ ተወስኗል ብለዋል።
እነዚህ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ሁለቱ ወጣቶች (ደንበኞቻቸው ) ዛሬ ከእስር ቤት ይወጣሉ ብለው ተስፋ
እንደሚያደርጉም የህግ ባለሙያው ተናግረዋል።
የአሜሪካ ዜግነት አለው የተባለው እና በእስር ላይ የሚገኘው  ሦስተኛው ግለሰብ ሚሻ ጪሪ የሚባል ሲሆን፤ የጃዋር መሐመድና የጽንፈኛ ኦሮሞ ብሔርተኞች ንብረት በሆነው የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦ.ኤም.ኤን) ቴክኒሺያን ሆኖ በመሥራት ላይ እንደነበር ታውቋል።
ሚሻ ጪሪ ፍርድ ቤት ቀርቦ በነበረበት ወቅት በጉዳዩ ላይ የአሜሪካን ኤምባሲን ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ጥረት እንዳልተሳካለት በመግለጽ ፖሊሶች ይህንን መብቱን እንዲያከብሩለት ጠይቆ ነበር።
በዶክተር ዳንኤል በቀለ የሚመራው  የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ትናንት የአስረኞችን ሁኔታ አስመልክቶ በዝርዝር ባወጣው መግለጫ ላይ ሦስቱም የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች እንቁላል ፍብሪካ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የሚገኘው ጊዜያዊ እስር ቤት ውስጥ እንዳሉ ይፋ አድርጓል።
ግለሰቦቹን አስመልክቶ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ፤ “በኢትዮጵያ የሚገኙ የአሜሪካዊያን ደህንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው” ሲል ጠቁሞ ፣ አሜሪካውያን በኢትዮጵያ ታስረው ከሆነ በተቻለ ፍጥነት እንደሚጎበኙ እና አስፈላጊው ድጋፍ እና አገልግሎቶች እንደሚያቀርብ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።

LEAVE A REPLY