በኢትዮጵያ ዛሬ 14 ሰዎች ሲሞቱ 720 ሰዎች ቫይረሱ በምርመራ ተገኝቶባቸዋል

በኢትዮጵያ ዛሬ 14 ሰዎች ሲሞቱ 720 ሰዎች ቫይረሱ በምርመራ ተገኝቶባቸዋል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ከፍተኛው የሞት መጠን የሆነው የ14 ሰዎች ሕልፈተ ሕይወት በዛሬው ዕለት ተመዘገበ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱ ከተነገረበት ከመጋቢት 4 ቀን አንስቶ እስካሁን ድረስ ባለው የአምስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ከፍተኛ ቁጥር ያለበት እለታዊ ሪፖርት ቀርቦ አያውቅም።
ባለፉት 24 ሰዐታት ውስጥ በተደረገው 9 ሺኅ 527  የላብራቶሪ ምርመራ ውስጥ 720 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውም የጤና ሚኒስትር ይፋ አድርጓል።
ዛሬ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ የ14 ሰዎች ህይወት ማለፉን ያረጋጡት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ፤ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 223 መድረሱን አስታውቀዋል።
በአንጻሩ ትናንት 250 ሰዎች ከኮሮና ቫይረስ ማገገማቸውን ተከትሎ በአጠቃላይ ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 6 ሺኅ 216 መድረሱን ከመግለጫው መረዳት ተችሏል።
 እስካሁን ድረስ 382 ሺኅ 339 ሰዎች ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑን የተናገሩት የጤና ሚኒስትሯ፤  በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች  ድምር ቁጥር 13 ሺኅ 968 ደርሷል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በምርመራ ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠው ሰዎች ቁጥር 7 ሺኅ 527 እንደሆነ ያስታወሰው የጤና ሚኒስቴር፤ ከታማሚዎቹ መሀል 65 ሰዎች በጽኑ የታመሙ ሕሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም አስታውቋል።

LEAVE A REPLY