በኮቪዲ-19 ምክነያት የተዘጋው አ/አ ዮንቨርስቲ 5 ሺኅ 600 የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችን አስመረቀ

በኮቪዲ-19 ምክነያት የተዘጋው አ/አ ዮንቨርስቲ 5 ሺኅ 600 የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችን አስመረቀ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ትምህርት ያቋረጠው የአዲስ አበባ ዮንቨርስቲ የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችን አስመረቀ።

ዛሬ ዮንቨርስቲው ያስመረቀው  በተለያየ የትምህርት ዘርፍ  ያስተማራቸውን ከ5 ሺኅ 600 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ፡፡
ከተመራቂዎቹ መካከል 244 በሦስተኛ ዲግሪ፣ 3 ሺኅ 128 በ2ኛ ዲግሪ፣  2 ሺኅ 370 በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸው ተገልጿል።
ተመራቂዎቹ ወቅታዊ የጤና ስጋት በሆነው ኮቪድ19  ምክንያት በቴሌቪዥን እና በዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ የትስስር ገጽ በተላለፈ ሥነ ሥርዓት ነው የተመረቁት፡፡
አዲስ አበባ ዮንቨርስቲ በወረርሽኙ ሳቢያ ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ ትምህርት መስጠት ቢያቋርጥም የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ቀሪ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉን ተከትሎ ተማሪዎቹ እንዲመረቁ ማድረጉ ተገቢ ቢሆንም የክልል ዮንቨርስቲዎችም ይህንን አሠራር የሚተገብሩ ከሆነ የትምህርት ጥራት ችግሩን ያባብሳል እየተባለ ነው።
 በተለይም በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት ዮንቨርስቲዎች ከዓመቱ የትምህርት ጅማሮ አንስቶ በብጥብጥና ኹከት ውስጥ መክረማቸውን ተከትሎ በተደጋጋሚ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ፣ ተማሪዎችም ወደየቤተሰቦቻቸው ለመመለስ መገደዳቸው ይታወቃል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል በተጨማሪ ከወርሃ መጋቢት ጀምሮ ዮንቨርስቲዎቹ መዘጋታቸው አስቀድሞ በብጥብጥና በብሔር ተኮር ግጭት የተጓተተውን ትምህርት የበለጠ አዳክሞታል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችን በዚህ ችግር ውስጥ እያሉ ማስመረቅ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል ይላሉ።

LEAVE A REPLY